ቀጥታ፡

ሁሉም ዜጋ ብዙሃነትን አምኖ በመቀበል እውቅና እንዲሰጠው ጥሪ ቀረበ

አርባ ምንጭ ጥር 4/2013 (ኢዜአ) በሀገሪቱ ዘላቂ ሠላምን ለማስፈን ሁሉም ዜጋ ብዙሃነትን አምኖ በመቀበል እውቅና እንዲሰጠው ጥሪ ቀረበ።

የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በሠላም፣ አብሮነት፣ በብዝሃነትና  በግጭት  አፈታት  ዙሪያ በአርባ ምንጭ ከተማ  ለባለድርሻ አካላት ያዘጋጀው  የምክከር  መድረክ   ተካሂዷል።

 የምክክር መድረክ ሲያበቃ የጉባዔ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት በሀገሪቱ  የሚስተዋሉ ግጭቶች ብዝሃነትን ካለመረዳት የሚከሰቱ ናቸው።

ለመፍትሄውም በብዙሃነት ላይ  የጋራ ግንዛቤ እንዲኖረን እንደሚያስፈል ገልጸው በተለይ ሁሉም ዜጋ ብዙሃነትን አምኖ በመቀበል እቅውና እንዲሰጠው ጥሪ አቅርበዋል።

ጉባዔው ይህንን ለማስረፅና ሀገሪቱ እያጋጠማት ያለው ግጭት እንዲቆሙ በህዝቦች  መካከል እርቀ ሰላም ለማውረድ ጥረት ሲያደርግ  መቆየቱን ተናግረዋል።

የአርባምንጮ መድረክም የዚሁ ጥረተ አካል መሆኑን ጠቅሰው  የጉባዔው ተሳታፊዎች  ልዩነት በተፈጥሮ የተቸረ ፀጋ መሆኑን በአግባቡ በመረዳት ለአካታችነት፣ ሚዛናዊነትና  ፍትሐዊነት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በተለይ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ያለው መስተጋብር  ተመጋጋቢና አንዱ የአንዱን ክፍተት የሚሞላ እንደመሆኑ ብዝሃነታችን መረዳትና እውቅና መስጠት ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የክልሎች ጉዳይ ኃላፊ መጋቢ ይታገሱ ኃይለሚካኤል በበኩላቸው በሀገሪቱ ያለው  የጾታ፣ ብሔር፣ ሐይማኖትና ቋንቋ ብዝሃነትን  ሰዎች  ያለመረዳትና እውቅና ያለመስጠት ችግር እንደሚስተዋል ተናግረዋል።

ሆኖም የብዝሃነት ምንጭ ፈጣሪ በመሆኑ ማንም ሊያስወግደው  ስለማይችል አምኖ መቀበል እንደሚበጅ ገልጸዋል።

በተለይ አንዱ ብሔር ወይም ኃይማኖት አንዱን አጥፍቶ መኖር የማይቻል በመሆኑ ብዝሃነትን ማክበር ጥቅሙ ለራስ ነው ብለዋል።

ከግጭት የሚገኝ ትርፍ የለም ያሉት መጋቢ ይታገሱ ከመተባበርና አንድነት ግን  ብዙ  እናተርፋለን ሲሉ አብራርተዋል።

ሌላው የሃይማኖት አባት ሊቀ ህሩያን ገሪማ ጌታነህ በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ  የተለያየ ብሔር  ብሔረሰቦችና ኃይማኖቶች መዲና በተለይም  የሰው ዘር መገኛ በመሆንዋ ተከባብሮ መኖር የሚጠቅም መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ በደስታና በሀዘን ለዘመናት ተሳስቦ ስለመኖሩ የአባቶቻችን ታሪክ ምስክር ነው ያሉት አስተያየት ሰጪ ሀገሪቱ በተለይ በኃይማኖት ምክንያት ከውጭ ተሰደው የመጡ ወገኖችን በመቀበል ያስተናገዱበት አኩሪ ታሪክ ያላት መሆኑን አውስተዋል።

አሁን ላይ የሚስተዋለው ውዥንብር የህዝቡን አንድነት እንዳይሸረሽረው   ለመከላከል   መንግስት መስራት እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል።

በምክክር መድረኩ ከጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ ዞኖች እና አሌ ልዩ ወረዳ የተውጣጡ  የሀይማኖት  አባቶችና  የሀገር ሽማግሌዎች ተሳተፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም