ቀጥታ፡

የዕደ ጥበብ አምራቾች ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበት አውደ ርዕይ ተከፈተ

አዲስ አበባ፣ ጥር 4/2013 (ኢዜአ) የዕደ ጥበብ አምራቾች ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበት አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ተከፈተ፡፡

የዕደ ጥበብ አምራቾች ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበት አውደ ርዕይ ዛሬ በአዲስ አበባ ተከፍቷል።

አውደ ርዕዩ "የአገሬ የዕደ ጥበብ ምርት" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ከተማ የባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አማካኝነት የተዘጋጀ ሲሆን፤ በመዲናዋ ሶስት ቦታዎች መካሄድ ጀምሯል፡፡ 

በአውደ ርዕዩ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተወጣጡት 150 አምራቾች ምርቶቻቸውን ይዘው ቀርበዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ በዚህን ወቅ የኢትዮጵያ መገለጫ የሆኑ የዕደ-ጥበብ ውጤቶች ለዓለም ገበያ በማቅረብ ኢትዮጵያን ማስተዋወቅ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ የዕደ-ጥበብ አማራቾች የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበት ምቹ ሁኔታ መመቻቸት እንዳለበትም ነው የተናገሩት።

የከተማ አስተዳደሩ በዚህ ረገድ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ የባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ወይዘሪት ፋይዛ መሀመድ በበኩላቸው ወቅቱ የጥምቀት በዓል የሚከበርበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አውደ ርዕዩ አምራቾችና ምርቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ቢሮው በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ቃል ገብተዋል።

አውደ ርዕዩ በአዲስ አበባ ስቴዲዬም፣ በፒያሳ ጊዮርጊስ አደባባይ እና በአራት ኪሎ ዳግማዊ ሚኒልክ ትምህርት ቤት አካባቢ ነው የተዘጋጀው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም