ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ ለቀበሌ መታወቂያ እድሳትና የጠፋባቸውን ለመተካት እየተጠየቀ ያለው ክፍያ የተጋነነ ሆኗል- ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፣ ጥር 4/2013 (ኢዜአ)  በአዲስ አበባ ከተማ ለቀበሌ መታወቂያ እድሳትና የጠፋባቸው ዳግም መታወቂያ ለማግኘት ከ80 እስከ 200 ብር ክፍያ መጠየቁ የሁሉንም አቅም ያላገናዘበ በመሆኑ ቅሬታ አሳድሮብናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።
የአዲስ አበባ ከተማ የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ከህዳር 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የቀበሌ መታወቂያ ለማግኘትና ለወሳኝ ኩነት አገልግሎቶች የክፍያ ማሻሻያ ተደርጓል።

በከተማው ካቢኔ የጸደቀውን የክፍያ ተመን ማሻሻያ መመሪያ በሁሉም ወረዳዎች ለህዝብ ይፋ መደረጉም ተገልጿል።

ሆኖም ማሻሻያው የበርካታውን ነዋሪ የኢኮኖሚ አቅም ያላገናዘበና ቅሬታ ያስከተለ መሆኑን አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በተደረገው ማሻሻያ መሰረት ለአዲስ መታወቂያና ነባሩን ወቅቱን ጠብቆ ለማሳደስ 80 ብር የሚጠይቅ ሲሆን ሳይታደስ የጊዜ ገደብ ላለፈበት እና ለጠፋ መታወቂያ ምትክ ለመስጠት 150 ብር እንዲከፈል ያስገድዳል።

አዲስ ዲጂታል መታወቂያ ለማግኘትና በወቅቱ ለማሳደስ ደግሞ የ100 ብር ክፍያ የሚጠይቅ ሲሆን ሳይታደስ ጊዜው ያለፈበት ከሆነ እና የጠፋ ከሆነ አዲስ ለማግኘት 200 ብር ያስከፍላል።

ሌሎች የወሳኝ ኩነት አገልግሎቶችም እንደ የአገልግሎት አይነቶች የክፍያ ተመን ላይ ጭማሪ መደረጉን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያሳያል።

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 የቀበሌ መታወቂያ ለማግኘት የመጡት ወይዘሮ ትዕግስት ይርጋሸዋ፣ አቶ አቤኔዜር እንዳለ እና አቶ አብረው ታደለ የተደረገው የአገልግሎት ክፍያ ማሻሻያ የህብረተሰቡን አቅም ያገናዘበ እንዳልሆነ ነው የገለጹት።

ወይዘሮ ትዕግስት ይርጋሸዋ እና አቶ አቤኔዘር እንዳለ ክፍያው የህዝቡን አቅም ያገናዘበ አለመሆኑን ተናግረዋል። 

አቶ አበረው ታደለ ቀደም ሲል ክፍያው  አምስት እና አስር ብር  ከነበረው ክፍያ 150 ብር መደረጉ ትክክል አይደለም ብለዋል።

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 የወሳኝ ኩነት የክብር መዝገብ ሹም አቶ ቴዎድሮስ ሰለሞን፤ የአገልግሎት ክፍያ ተመን ጭማሪው በከተማ አስተዳደሩ መመሪያው ፀድቆ መምጣቱን ይናገራሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታከለ ነጫ፤ ለመታወቂያና የወሳኝ ኩነት አገልገሎቶች የክፍያ ማስተካከያ መደረጉን ገልጸዋል።

ማሻሻያው የተደረገው "መታወቂያ ለመስራት ለሚጠቀሙባቸው ቁሳቁሶችና የመታወቂያው የአገልግሎት ጊዜ ለሁለት ዓመት ብቻ የነበረው ወደ 4 ዓመት ከፍ እንዲል በመደረጉ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

በመታወቂያና የወሳኝ ኩነት አገልገሎት ክፍያ ከዚህ ቀደም የነበረውን ዋጋ ይዞ መቀጠል የማይቻል መሆኑንም አብራርተዋል።

ለመታወቂያና ሰርተፍኬት የሚወጣው ግብዓት ዋጋው በጣም ጨምሯል፤ በመሆኑም ከወጪው አንጻር የግድ የዛሬ 10 ዓመት 20 ዓመት የነበረውን ዋጋ ይዞ መቀጠል አይቻልም ነው ያሉት።

አዲሱ የአገልግሎት ክፍያ ተመን ማሻሻያ የነዋሪዎች አቅም ያገናዘበ አይደለም በሚል ለሚነሳውም ቅሬታ "አቅም የሌላቸው ዜጎች በነፃ የሚስተናገዱበት አሰራር ተመቻችቷል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም