ቀጥታ፡

በማዕድን ዘርፉ በስፋት የሚስተዋለው ሙስና ለዘርፉ እድገት እንቅፋት መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ

አዲስ አበባ ጥር 4/2013 (ኢዜአ) በማዕድን ዘርፉ በስፋት የሚስተዋለው ሙስና ለዘርፉ ልማትና አገራዊ እድገት አስተዋፅኦ እንቅፋት መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ባለፉት አምስት ወራት 4 ሺህ 100 ኪሎ ግራም ወርቅ በመግዛት ከ300 ሺህ ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱም ተገልጿል።

የፌዴራል የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ከአንድ ዓመት በፊት በማዕድን ዘርፉ የሚያጋጥሙ ሙስና እና ብልሹ አሰራሮችን አስመልክቶ ያስደረገውን ጥናት ይፋ አድርጓል።

ጥናቱ አዲስ አበባን ጨምሮ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ትግራይ ፣አፋርና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎችን ያካተተ እንደነበርም ተመልክቷል።

የሴንተር ኦፍ ኤክሰለንስ አለም አቀፍ አማካሪ ስራ አስኪያጅ ጌዲዮን ጃለታ፤ የጥናት ውጤቱን ይፋ ባደረጉበት ጊዜ በኢትዮጵያ የመልካም አስተዳደርና የኢ-ፍትሃዊነት ችግሮች አንዱ መነሻ በማዕድን ዘርፉ ያለው ብልሹ አሰራር ነው ብለዋል።

በዘርፉ ከፍቃድ አሰጣጥ እስከ ማዕድን ሽያጭ ያሉት ሰንሰለቶች በሙስና እና ብልሹ አሰራር የተተበተበ መሆኑንም ገልጸዋል።

''በጉምሩክ በኩል ቁጥጥር የሚደረገው ወርቅ ላይ ብቻ መሆኑ ሌሎች ማዕድናት በቀላሉ እንዲወጡ ያደርጋል'' ያሉት አቶ ጌዲዮን፣ ገቢዎች ሚኒስቴርም በማዕድን ዘርፍ ፍቃድ ያላቸው ኩባንያዎች ላይ በመቆጣጠር ክፍተት አለበት ብለዋል።

በዘርፉ ብልሹ አሰራሮች እንዳሉ ቢታወቅም፤ ከወረዳ ጀምሮ ያሉ አመራሮች እጃቸው ስላለበት ዝምታን ይመርጣሉም ብለዋል።

መንግስት አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ላይ ለማዕድን ዘርፉ ትኩረት የሰጠ ቢሆንም፤ አተገባበሩ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ካልተሰራ የሚፈለገው ውጤት እንደማይመጣ ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል።

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ፤ ማዕድን አላቂ የተፈጥሮ ሃብት እንደመሆኑ በአግባቡ መጠቀም ካልተቻለ በድህነት ውስጥ መቆየት ግድ ይላል ብለዋል።

ዘርፉ የዜጎችን ህይወት በዘላቂነት እንዳያሻሽልና ለአገሪቷ ምጣኔ-ሃብት ዕድገት ድርሻውን እንዳይወጣ ማድረጉን አመልክተዋል።

የጥናቱ ግኝቶች ትክክለኛ በመሆናቸው መስሪያ ቤታቸው ችግሮቹን ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በተለይም የማዕድን ፍቃድ ቁጥጥር ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኩል ይታይ የነበረው የወርቅ ግዥ መሻሻል ማሳየቱንና የወርቅ መግዣ ማዕከላት መስፋፋታቸውንም ነው ወይዘሮ ስመኝ የተናገሩት።

ባለፉት አምስት ወራትም ባንኩ 4 ሺህ 100 ኪሎ ግራም ወርቅ መግዛቱንና ከዚህም ከ300 ሺህ ዶላር በላይ መገኘቱን ገልጸዋል።

ጥናቱ ከአንድ ዓመት በፊት የተደረገ በመሆኑ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ጨምሮ መንግስት ዘርፉን ለማዘመን እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችን አለማካተቱ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም