ቀጥታ፡

ግብጽና ሱዳን የሶስትዮሽ ድርድሩን በማስተጓጎል ድርድሩን ከአፍሪካ ህብረት የማውጣት ፍላጎት አላቸው- አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

አዲስ አበባ ጥር 4/2013 (ኢዜአ) ግብጽና ሱዳን የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድሩን በማስተጓጎል ከአፍሪካ ህብረት ወደ ተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የመውሰድ ፍላጎት እንዳላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።

የህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል የሚጥሩ ሃይሎች ስለመኖራቸውም ጠቅሰዋል።

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ በሀገሪቱ ወቅታዊ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች አበይት የዲፕሎማሲ ክንውኖችን አስመልክተው ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የሱዳን ወታደራዊ ኃይል ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቆ በመግባት ህገ ወጥ እንቅስቃሴ እያደረገ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ከ100 ዓመት በፊት ከተደረገው የድንበር ስምምነት በኋላ በአውሮፓዊያኑ አቆጣጥር 1972 በሁለቱ አገሮች ዳግም ለማካለል የጋራ ኮሚቴዎች ተቋቁመው እንደነበር አስታውሰዋል።

በ1972ቱ ስምምነትም የድንበር ማካለል ስራው እልባት እስኪያገኝ ከ100 ዓመት በፊት በነበረው ድንበር እንዲቆዩ ስምምነት እንደነበርና ስምምነቱም በአፍሪካ ህብረትና በመንግስታቱ ድርጅት ተቀምጧል ብለዋል።

ያም ሆኖ በሱዳን በኩል ከዓመታት በፊት የተደረሰውን ስምምንት በመጣስ ዓለም ቀፍ ህግን የሚጥስ፣ ሁለቱን አገሮች የማይጠቅምና በሌሎች ሃይሎች የሚገፋ ህገ ወጥ እንቅስቃሴ እንዳለ ገልጸዋል።

በተለያዩ ጊዜያት የተጀመሩ በጋራ ድንበር ኮሚሽን የድንበር ማካለል ስራዎች በመመለስ የሁለቱን አገራት የድንበር ችግር በሰላም መፍታት በኢትዮጵያ በኩል ቅድሚያ የሚሰጠው እርምጃ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያና ሱዳን ሕዝቦች የረጅም ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው ያነሱት አምባሳደር ዲና የጋራ ዕድገትና ተጠቃሚነት እንጂ ጦርነት እንደማይሹ ገልጸዋል። 

ይሁን እንጂ  የሱዳን ጦር በተጠናከረ ሁኔታ ድንበር የመግፋት እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን አብራርተዋል።

በዚህ ዙሪያ ኢትዮጵያ እስካሁን በትግስት የምትመለከተው ለሠላምና ዲፕሎማሲ ቅድሚያ የምትሰጥና ዓለም አቀፍ መርህን የምትከተል በመሆኗ ነው ብለዋል።

የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ በመግባት እያደረገ ያለውን ሕገ ወጥ እንቅሰቃሴ ኢትዮጵያ መታገሷ ከፍርሃት ሳይሆን "የሌሎችን ሃይሎች የጨዋታ ካርድ ላለመምዘዝ ነው" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋረ ወደ ግጭት እንድትገባ በተለይም ከሱዳን ጋር ወደ ጦርነት በማስገባት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሶስተኛ ወገኖች ፍላጎት እንዳለ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያን ወደ ትርምስ በማስገባት ልማቷን አንዳትቀጥል በተለይም የህዳሴ ግድብ እንዲስተጓጎል የሚሹ ሃይሎች እንዳሉ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ሁሌም በዲፕሎማሲ እንጂ በጦርነት ችግሮች ይፈታሉ የሚል እምነት እንደሌላት ገልጸው፣ ከጀርባ የሚገፉ ወገኖችን ካርድ እንደማትጫወትም አረጋግጠዋል።

በአፍሪካ ህብረት በኩል ዳግም የተጀመረው የህዳሴ ግድብ የሶስተዮሽ ድርድር ግብጽ የማደራደሪያ ሰነዱን ውድቅ ብታደርገውም በእስካሁኑ ድርድር የነበሩ አንድነትና ልዩነቶች እንዲቀርቡ ላለፈው እሁድ ቀጠሮ እንደነበር አስታውሰዋል።

በዚህም በአደራዳሪው አካል በተሰየሙ ባለሙያዎች የቀረበው ሰነድ ላይ በሶስቱ አገሮች ሚኒስትሮች ውይይት መደረጉን፤ በመጨረሻም ሱዳን ከአፍሪካ ኤክስፐርቶች ጋር በግል መደራደር አለብኝ ማለቷን ገልጸዋል።

በአፍሪካ ህብረት በኩል በቀረበው የድርድር አማራጭ አይነተ ብዙ ሰበብ በመደርደር ሱዳንና ግብጽ ተራ በተራ ድርድሩ እንዲስተጓጎል እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የሚደረገውን የሶሰትዮሽ ድርድር ግብፅና ሱዳን ወደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ለመውሰድ ፍላጎት እንዳላቸውም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ግን አሁንም ቢሆን ሶስቱም አገራት አሸናፊ የሚሆኑበት የአፍሪካን ጉዳይ በአፍሪካ ለመፍታት በአፍሪካ ህብረት ድርድር ዳር እንዲደርስ የጸና አቋም እንዳላት ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ኢትዮጵያ በሰሜን ኢትዮጵያ ከህግ ማስከበር በኋላ እያደረገች ያለችውን የመልሶ ግንባታና ሰብዓዊ ርዳታ አቅርቦት በተመለከተ ለውጭ ማህበረሰብ ማብራሪያ ስለመስጠታቸውም አምባሳደር ዲና አንስተዋል።

ሌሎች የቢዝነስና ኢንቨስትመንት፣ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ እንዲሁም የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ተግባራት ባሳለፍነው ሳምንት ስለመከወናቸው አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም