ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ጨዋታ ጅማ አባቡና የሀበርቾ ዱራሜ አቻውን አሸነፈ

ጅማ ሀምሌ 16/2010 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ  "ለ" ምድብ  25 ሳምንት ጨዋታ ጅማ አባቡና ዛሬ በሜዳው የሀበርቾ ዱራሜ አቻውን አስተናግዶ አንድ ለባዶ አሸነፈ፡፡ ጅማ አባቡና ያሸነፈው መደበኛው የጨዋታ ጊዜ ከተጠናቀቀ በኋላ ዳኛው በጨመሩት የባከነ ስድስት ደቂቃ ውስጥ ቴዎድሮስ ታደስ ባስቆጠረው  ብቸኛ ጎል  ነው፡፡ አባቡና በማጥቃት ላይ የተመሰረተ ጨዋታ ቢመርጥም የተሳካ ሙከራ በማድረግ በኩል ሀበርቾ ዱራሜ  የተሻለ ነበር ፡፡ የሀበርቾ ዱራሜ ቡድን   ከእረፍት በፊትና በኋላ በመልሶ ማጥቃት ሁለት ያለቀላቸው የግብ ሙከራዎች አድርጎ  በአባቡናው ግብ ጠባቂ  ከሽፎበታል፡፡ በውድድሩ ወቅት  ከጅማ አባቡና  አንድ በሃበርቾ በኩል ደግሞ አራት ተጫዋቾች ቢጫ ካረድ  ሲመለከቱ  ሌላ አንድ ተጨዋች ደግሞ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል፡፡ አባቡና  ዛሬ አሸንፎ ሙሉ ነጥብ ይዞ መውጣቱ  ወደ ኢትዮጵያ ፕርሚየር  ሊግ ለመመለስ ለሚያደረገውን ጥረት ያግዘዋል፡፡ አሁን ላይ ጅማ አባቡና  ከደቡብ ፖሊስ ጋር በእኩል 47 ነጥብ በጎል ክፍያ ተበላልጠው ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን የኢትዮያ ከፍተኛ ሊግ ሊጠናቀቅ አምስት ጨዋታዎች እንደሚቀሩት ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም