በነቀምቴ ከተማ 1ሺህ126 ሴቶች በቁጠባ ማህበር ተደራጅተው እራሳቸውን ለመቻል እየተንቀሳቀሱ ነው

55

ነቀምቴ ጥር 04/2013 (ኢዜአ) በነቀምቴ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ 1ሺህ126 ሴቶች በቁጠባ ማህበር ተደራጅተው እራሳቸውን ለመቻል እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን የከተማዋ አስተዳደር የሴቶች፣ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ጽህፈት ቤት ገለጸ ፡፡
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ መስከረም ዓለማየሁ እንዳስታወቁት እነዚህ  በጥቃቅንና አነሰተኛው የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ሴቶች ከሚያገኙት ገቢ ቆጥበው ኑሮቸውን እንዲያሻሽሉ በቁጠባ ማህበራት እንዲደራጁ ተደርጓል፡፡

መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማስተባበር ሴቶች ከወለድ ነፃ የሆነ የብድር በማግኘት ሰርተው ራሳቸውን እንዲችሉ ጽህፈት ቤቱ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ  በተያዘው በጀት ዓመት 3ሺህ ሴቶችን በቁጠባ አገልግሎት ለማደራጀት ታቅዶ ባለፉት ስድስት ወራት  1ሺህ126  ሴቶችን በ68 ማህበራት  በማደራጀት ወደ ቁጠባ ሥራ ማስገባት መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በስድስት ወራት ውስጥም   261ሺህ892 ብር መቆጠብ መቻላቸውንም ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡

በቁጠባ ማህበር ከተደራጁት መካከል በከተማዋ የቀበሌ አራት ነዋሪ ወይዘሮ ምትኬ በሊና በሰጡት አስተያየት በማህበራቸው በኩል ከሚያገኙት ገቢ  በየሁለት ሳምንት 30 ብር እየቆጠቡ እንደሚገኙ ተናገረዋል።

ከቆጠቡት ገንዘብ እየተበደሩም በመስራት ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን እያስተዳደሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አሊማ ሁሴን በበኩላቸው አባታቸውን ያጡ ልጆቻቸውን በሰው ቤት እየኖሩና እየሰሩ ሲያሳድጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በቁጠባ ማህበሩ በመደራጀት ባገኙት ብድር ሰርተው ራሳቸውን በመቻል መኖሪያ ቤት ተከራይተው መኖር መጀመራቸውን  አስረድተዋል፡፡

ተደራጅተው ሰርተው ከሚያገኙት ገቢ በመቆጠብ  ከጠባቂነት በመላቀቅ እራሳቸውን እየቻሉ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ  ሌላዋ  የከተማዋ ነዋሪ   ወይዘሮ ፋንታዬ ጨመዳ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም