ቀጥታ፡

በአገሪቷ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥና የሠላምና ዴሞክራሲ ግንባታው እንዲፋጠን ፖሊስ ሁሌም ዝግጁ ነው - ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል

አዲስ አበባ፣ ጥር 3/2013(ኢዜአ) በአገሪቷ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥና የሠላምና ዴሞክራሲ ግንባታው እንዲፋጠን ፖሊስ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ኃላፊነቱን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ፡፡

የፌዴራል፣ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ፓሊስ ኮሚሽነሮች 12ኛ የጋራ ጉባዔ በቢሾፍቱ እየተካሄደ ነው።

ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ በጉባዔው ላይ እንደገለጹት አገሪቷ የጀመረችው ለውጥ ከግብ እንዲደርስ የፖሊስ ሚና ከፍተኛ ነው።

በመሆኑም በአገሪቷ የሠላምና የዴሞክራሲ ግንባታ ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ፖሊስ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ጎን ለጎንም የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ፖሊስ ሥራውን እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።

የህወሓት ጁንታ በአገሪቷ ላይ ደቅኖት የነበረውን ፈተና ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር በመቀናጀት ድል ማድረጉንም አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዋነኛ ጠላቶች ገሚሶቹ መደምሰሳቸውንና ቀሪዎቹም በቁጥጥር ሥር እየዋሉ መሆኑን ጠቁመዋል።

ያም ሆኖ ዘላቂ ሠላም እንዲረጋገጥ የአገሪቷን ፓሊስ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ይሰራል ያሉት ኮሚሽነር ጄኔራሉ በቀጣይ ፖሊስ በብሔር የሚወሰን ሳይሆን ለሁሉም የሰው ልጆች ክብር የሚያገለግልበት ሁኔታ እንደሚመቻች ተናግረዋል።

የህወሓት ጁንታ እንደተደመሰሰው ሁሉ የአገሪቷን ሠላም የሚያደፈርሱ አካላትን ለመከላከልና ሠላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው "ኢትዮጵያ እንደ አገር እንድትቀጥል መስዋዕትነት የሚከፍልላት ሠራዊት ያስፈልጋታል" ብለዋል።

ይህንንም የመከላከያ ሠራዊት አባላትና የፌዴራል ፖሊሶች በተግባር ማስመስከራቸውን ገልጸዋል።

የሕግ የበላይነት እንዲከበርና እኩልነት እንዲረጋገጥ የፖሊስ ሚና የላቀ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በአገሪቷ ያሉ የጸጥታ ተቋማት ተቀናጅተው ኢትዮጵያ እንድትቀጥል በማድረጋቸውም ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

በአገሪቷ የሕግ የበላይነት ተረጋግጦና ሠላም ሰፍኖ እንድትቀጥል የፍትህ ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የሕግ የበላይነት ጉዳይ በምኞት ብቻ ሳይሆን መስዋዕትነት ያስፈልጋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ ነገ የሚመጣውን መስዋዕትነት ለመቀበልና ኢትዮጵያን እንደ አገር ለማስቀጠል የፖሊስ ሃላፊነት ከፍያለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጸጥታ ተቋማት አሰራርን ለማዘመን በቴክኖሎጂ እንዲደራጅ በሰው ሃይሉም እንዲጠናከር የሚሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ጉባዔው ነገም የሚቀጥል ሲሆን በክልል ፓሊስ ኮሚሽን ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ ላይ ውይይት እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

የ6ኛውን አገራዊ ምርጫ ቅድመ ዝግጅት የሚያመለክት ዕቅድም በነገው ዕለት የሚቀርብ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም