ቀጥታ፡

ወላይታ ድቻ የአሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀን ኮንትራት በሁለት ዓመት አራዘመ

አዲስ አበባ ሀምሌ 16/2010 የወላይታ ድቻ እግር ኳስ ክለብ የአሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀን የኮንትራት ውል በሁለት ዓመት ማራዘሙን አስታወቀ። የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ሆሲሶ ለኢዜአ እንደገለጹት ክለቡ ከአሰልጣኙ ጋር ዛሬ ባደረገው ውይይት ኮንትራቱ በሁለት ዓመት እንዲራዘም አድርጓል። አሰልጣኝ ዘነበ ቆይታው በአንድ ዓመት ብቻ እንዲራዘም ጥያቄ ቢያቀርብም ክለቡ አሰልጣኙ አብሮት እንዲቆይ ባለው ፍላጎት መሰረት ከአሰልጣኙ ጋር በመስማማት ለሁለት ዓመታት ከክለቡ ጋር እንዲቆይ ከስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል። አሰልጣኝ ዘነበ በቀጣይ የውድድር ዓመት ክለቡ በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከነበረበት የወራጅ ቀጠና ስጋት ሳይሆን በተሻለ መልኩ ቡድኑን ተፎካካሪ ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርግ ገልጿል። ለዚህ ይረዳው ዘንድ ዛሬ ከቡድኑ ተጫዋቾች ጋር ውይይት እንደሚያደርግና ክለቡን በተሻለ ደረጃ ተፎካካሪ ያደርጋሉ ብሎ የሚያስባቸውን ተጫዋቾች እንደሚያስፈርምም ተናግሯል። አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ በ2010 ዓ.ም የውድድር አጋማሽ ከክለቡ የተሰናበቱትን አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን በመተካት መረከባቸው የሚታወስ ነው። በዘንድሮው ዓመት ቆይታቸው ቡድኑ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ 32 ውስጥ እንዲገባ በማድረግ መልካም ጉዞ ያደረጉ ሲሆን በውድድሩ ዛማሌክን በማሸነፍ ትልቅ ውጤት አስመዝግበዋል። ያም ቢሆን ክለቡ በ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እስከመጨረሻው ሰዓት የመውረድ ስጋት የነበረበት ቢሆንም በ30ኛው ሳምንት ጨዋታ ወልዲያ ከተማን 3 ለ 0 በማሸነፍ ከመውረድ ተርፏል። ወላይታ ድቻ በፕሪሚየር ሊጉ 35 ነጥብ በመሰብሰብ 11ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም