ቀጥታ፡

የቼስ የሁለተኛ ደረጃ የዳኝነት ስልጠና ዛሬ ተጀምሯል

አዲስ አበባ ግንቦት 4/2010  ከዛሬ ጀምሮ እስከ ግንቦት 13 ቀን 2010 ዓ.ም የሚቆይ የቼስ ስፖርት የሁለተኛ ደረጃ የዳኝነት ስልጠና በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ተጀምሯል። ስልጠናው ላይ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ 15 ዳኞች በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙና ስልጠናው የሚሰጠው ዓለም አቀፍ የቼስ ዳኛ (አርቢትር) የሆነው ደጀኔ ዘላለም ነው። የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሰይፈ በላይነህ እንደተናገሩት፤ ስልጠናውን የሚወስዱት ዳኞች ከዚህ በፊት የአንደኛ ደረጃ የዳኝነት ስልጠና ወስደው በስራ ላይ የሚገኙ ናቸው። ለዳኞች በቼስ ውድድር ላይ ስላሉ ህጎችና መርሆዎች የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠና እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል። የሁለተኛ ደረጃ የዳኝነት ስልጠናው ክልሎች ውድድር ሲያዘጋጁ የሚያጋጥማቸውን የዳኞች ቁጥር ማነስ ችግር በመፍታት ረገድ የበኩሉን አስተጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። ክልሎች ውድድር በሚያዘጋጁበት ወቅት ዳኛ ስለሚያንሳቸው ከአዲስ አበባ ዳኞች እንደሚመደብላቸው ገልጸው የሚሰለጥኑት ዳኞች ይህን ችግር በተወሰነ ደረጃ ይፈቱታል ተብሎ ይጠበቃል። የሁለተኛ ደረጃ ስልጠናውን የሚወስዱት ዳኞች በቀጣይ የዓለም አቀፉ የቼስ ፌዴሬሽንና የአፍሪካ የቼስ ኮንፌዴሬሽን በሚያዘጋጇቸው ስልጠናዎች ላይ የመሳተፍ እድል እንደሚያገኙ ጠቁሟል። ትልቁ የቼስ ዳኝነት ደረጃ በዓለም አቀፉ የቼስ ፌዴሬሽን የሚሰጠው ዓለም አቀፍ አርቢትር ሲሆን ይህን ደረጃ ያገኘ ዳኛ በአህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች የትኛውንም አይነት ውድድሮች መምራት ይችላል። ቼስ በዓለም ላይ ከሚገኙ የቤት ውስጥ ስፖርቶች አንዱ ሲሆን ከግማሽ ቢሊዮን በላይ ሰዎች ያዘወትሩታል። ከጨዋታነቱ ባሻገርም የሰውን ልጅ አዕምሮ የማስፋት አቅም እንዳለውና በተለይም ሕፃናት ትምህርታቸው ላይ ትኩረት እንዲሰጡ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ይነገራል። በኢትዮጵያ በ16ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ አፄ ልብነ ድንግል፤ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ደግሞ የሸዋው ንጉሥ ሳህለ ስላሴ ቼስን ይጫወቱ እንደነበር ይነገራል።
 
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም