የካፍ አካዳሚን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዲያስተዳድር እና እንዲጠቀምበት ፍቃድ አገኘ

አዲስ አበባ ሐምሌ 16/2010 በአዲስ አበባ በተለምዶ ሀያት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘውን የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (ካፍ) አካዳሚ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዲያስተዳድርና እንዲጠቀምበት ፈቃድ ማግኘቱን ገለጸ። ሐምሌ 15 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ የአካዳሚው ስራ አስኪያጅ አቶ ሳህሉ ገብረወልድና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በካፍ ተወካይ ማግዲ አብዱራዛቅ አረካባቢነት የፊርማ ስነ ስርአት መካሄዱን አስታውቋል። በዚሁ መሰረት ፌዴሬሽኑ የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (ካፍ) አካዳሚን እንዲያስተዳድረውና እንዲጠቀምበት ከካፍ ፍቃድ ማግኘቱንና በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ የንብረት ርክክብ አድርጎ ስራ ይጀምራል። የካፍ አካዳሚ ግንባታ በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ በ1997 ዓ.ም ተጀምሮ በክትትል ማነስ ግንባታው እስካሁን እንደተጓተተ ነው። ስራው ሲጀመር ካፍ የግንባታ ስራውን ለግብፃውያን ተቋራጮች የሰጠ ቢሆንም፤ በተለያዩ  ምክያቶች ግንባታውን በማዘገየታቸውና በተፈለገው ጥራት ደረጃ ባለመስራታቸው ውሉ እንዲቋረጥ ተደርጎ ለኢትዮጵያውያን ተቋራጮች እንዲሰጥ መደረጉ ይታወሳል። ኢትዮጵያውያን ተቋራጮች የጀመሯቸውን ህንጻዎች ያጠናቀቁ ቢሆንም የእግር ኳስ ሜዳው ግን “የውሃ ችግር ገጥሞናል” በሚል ምክንያት ውላቸውን አቋርጠዋል። እስካሁን ባለው ሁኔታ የአካዳሚው የስፖርተኞች የመኝታ ክፍሎች፣ የስልጠና  ክፍሎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተጠናቀዋል። ይሁን እንጂ  በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ ሳር ለመስራት የታሰበው ሁለቱ የእግር ኳስ ሜዳዎች ገና በጅምር ላይ ናቸው። በሁለት ምዕራፍ የሚካሄደው የአካዳሚው ግንባታ የመጀመሪያው ምዕራፍ ስራ ተጠናቆ የሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ በመካሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን ግንባታው መቼ እንደሚያልቅ የተቀመጠ የጊዜ ገደብ የለም። የካፍ ፕሬዝዳንት አህመድ አህመድ ሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም በኢትዮጵያ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት አካዳሚውን ሲጎበኙ በተቻለ አቅም በፍጥነት ተጠናቆ ወደ ስራ እንዲገባ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸው ነበር። ካፍ በኢትዮጵያ እያስገነባ ያለው የስፖርት አካዳሚ በዋናነት በመካከለኛና ምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የተለያዩ ስፖርታዊ ስልጠናዎች የሚሰጥበትና ውድድሮች የሚካሄዱበት እንደሚሆን ይጠበቃል። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ከዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽን (ፊፋ) ጋር በመነጋገር ለሚሰጣቸው የዳኞች፣ የስፖርት አስተዳደር ስልጠና እና መሰል ሥልጠናዎች በአካዳሚው ይሰጣሉ። በ1957 ዓ.ም የተመሰረተው ካፍ ከኢትዮጵያ ውጭ በካሜሮን አንድ አካዳሚ ለአገልግሎት ክፍት ያደረገ ሲሆን በሴኔጋልም የስፖርት አካዳሚ በማስገንባት ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም