አገራዊ የጋራ አመራር መገንባት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ - ኢዜአ አማርኛ
አገራዊ የጋራ አመራር መገንባት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ ጥር 3/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩትና የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ አገራዊ የጋራ አመራር መገንባት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።
ተቋማቱ በስምምነቱ በመታገዝ በአመራር ግንባታ፣ በካይዘን ትግበራ፣ በወቅታዊ አገራዊና ዓለምአቀፋዊ ጉዳዮች በጋራ ይሰራሉ፡፡
በለውጥ ትግበራ፣ በምርምር፣ በትምህርትና ስልጠና በመታገዝ አገራዊ ሃላፊነትን መወጣት በስምምነቱ ይተገበራል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ያኢ ስምምነቱ “በጋራ አመራር ግንባታችን በመታገዝ በሀገር በቀል ዕውቀት የበለፀገና ዓለምአቀፋዊ ተሞክሮን ታሳቢ ያደረገ አመራር ለማፍለቅ ይረዳል” ብለዋል።
ይህም የመተባበር እሴቶቻችንን አጠናክሮ የሚያስቀጥል አመራር ከማስገኘቱ ባለፈ የሕዝብን የመበልጸግ ፍላጎትና የመንግስትን ምላሽ የመስጠት አቅም በማሳደግ ለስኬት የሚጥር አመራር ለመፍጠርም እንዲሁ።
በአገሪቷ ተመራማሪዎች የሚቀርቡ ስራዎች ቢኖሩም ከምርምር እስከ ትግበራው ያለው የአመራሩ ተሳትፎና ድጋፍ ውስን መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ ናቸው።
በስምምነቱ መሰረት አመራሩ የሚቀርቡለትን የምርምር ስራዎች ተግባራዊ በማድረግ አገራዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ሚናውን እንደሚያሳድግለት ጠቁመዋል።
አካዳሚው በምስራቅ አፍሪካ የላቀ የምርምር የልህቀት ማዕከል ለመሆን የያዘውን ግብ እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎች፣ በዘመናዊ የካይዘን አሰራር የተካነ ባለሙያና አመራር መፍጠርና ቀልጣፋ የጋራ ፖሊሲና ስትራቴጂ ትግበራ ከተቋማቱ የሚጠበቁ ውጤቶች ናቸው።
እነዚህን ውጤቶች ታሳቢ በማድረግ ተቋማቱ የጋራ አሠራርና ተልዕኮ፣ የስምምነት ሠነድ እንዲሁም በጥናት፣ ምርምርና በካይዘን አተገባበር ዙሪያ ለባለሙያዎቻቸው ስልጠና መስጠታቸው ተገልጿል።
በቀጣይም አገር አቀፍ የካይዘን ክፍተት ልየታ ማካሄድ፣ የጥናትና ምርምር አጀንዳዎችን መቅረጽና ድጋፍ ለማግኘት የሚረዱ ፕሮጀክቶች ፕሮፖዛሎችን በጋራ እንደሚያዘጋጁ አስታውቀዋል።
ከሁለቱ ተቋማት 51 ባለሙያዎች በካይዘን ጥቅል እይታ፣ በምርምር ምንነት፣ በፕሮጀክት ፈንድ አዘገጃጀትና አስተዳደር ላይ የጋራ ስልጠና ማግኘታቸውን ለማወቅ ተችሏል።