ቀጥታ፡

ሉሲዎቹ በሴካፋ የሴቶች እግር ኳስ ውድድር ሁለተኛ ጨዋታቸውን ዛሬ ከሩዋንዳ ጋር ያደርጋሉ

አዲስ አበባ ሐምሌ 16/2010 በሩዋንዳ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው ሶስተኛው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) የሴቶች እግር ኳስ ውድድር የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከአዘጋጇ አገር ሩዋንዳ ጋር ዛሬ ሁለተኛ ጨዋታውን ያደርጋል። ሐምሌ 12 ቀን 2010 ዓ.ም በተጀመረው በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ አዘጋጇ ሩዋንዳ ፣ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያና ኬንያ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ። ሉሲዎቹ ከትናንት በስቲያ ከኡጋንዳ አቻቸው ጋር ባደረጉት ጨዋታ ሁለት ለአንድ መሸነፋቸው የሚታወስ ነው። ዛሬ ሁለተኛ ጨዋታቸውን ከቀኑ 10 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ከአዘጋጇ አገር ሩዋንዳ ጋር በአገሪቷ ብሔራዊ ስታዲየም የሚያደርጉ ሲሆን ጨዋታውን ካሸነፉ ወደ ዋንጫው ፉክክር መመለስ ይችላሉ። የምስራቅ አፍሪካ መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሽንፈት ተከትሎ ውድድሩን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት ያገኘው ብሔራዊ ቡድን በኡጋንዳ ተሸነፈ በሚል የተለያዩ ዘገባዎችን ሲያሰራጩ ነበር። የኡጋንዳ ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያ ጨዋታው ታንዛንያን 1 ለ 0 ያሸነፈ ሲሆን ይህንን ጨዋታ ኢትዮጵያዊቷ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ በመሐል ዳኝነት፤ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ወጋየሁ አበራ በረዳትነት መምራታቸው የሚታወስ ነው። ከሉሲዎች ጨዋታ በፊት ከቀኑ 8 ሰዓት ላይ ኡጋንዳ ከታንዛኒያ ይጫወታሉ። በአሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ የሚሰለጥነው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ቀጣይ ጨዋታውን ከነገ በስቲያ ከኬንያ ጋር ከቀኑ 8 ሰዓት ላይ የሚያደርግ ይሆናል። በአጠቃላይ አምስቱ አገራት እርስ በእርስ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች የተሻለ ነጥብ ያስመዘገበ ቡድን የውድድሩ አሸናፊ እንደሚሆን የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ የክለቦች ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) አስታውቋል። በዚሁ መሰረት ኡጋንዳ ያደረገቻቸውን ሁለት ጨዋታዎች በማሸነፍ ስድስት ነጥብ በማግኘት እየመራች ሲሆን አዘጋጇ ሩዋንዳ ያደረገችውን አንድ ጨዋታ በማሸነፍ ሶስት ነጥብ በመያዝ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ኬንያና ታንዛንያ ሁለት ጨዋታ አድርገው ሁለቱም በተመሳሳይ በአንዱ ተሸንፈው በአንዱ አቻ ወጥተው ተመሳሳይ አንድ ነጥብ ብቻ የያዙ ሲሆን ኢትዮጵያ አንድ ያደረገችውን ጨዋታ ተሸንፋ ያለ ምንም ነጥብ መጨረሻ ደረጃ ላይ ትገኛለች። የሴካፋ የሴቶች እግር ኳስ ውድድር እስከ ሐምሌ 20 ቀን 2010 ዓ.ም ይቆያል። የሴካፋ ሴቶች እግር ኳስ ውድድር እ.አ.አ በ1986 ለመጀመሪያ ጊዜ ሲካሄድ ዛንዚባር ውድድሩን ያሸነፈች ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊት በኡጋንዳ በተካሄደው ውድድር ታንዛንያ አሸናፊ መሆኗ ይታወሳል። በኡጋንዳ በተካሄደው ውድድር የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሉሲዎች አዘጋጇ ኡጋንዳን አራት ለአንድ በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁበት ከፍተኛ ያስመዘገቡት ውጤታቸው ነው። የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ የክለቦች ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ)የሴቶች እግር ኳስ ውድድር ለማዘጋጀት የበጀት ችግር እየገጠመው ውድድሩ ለረጅም ጊዜያት ሳይካሄድ ቆይቷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም