ቀጥታ፡

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሰላም ለማምጣት የድርሻውን ሊወጣ ይገባል-የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ

አርባምንጭ ጥር 3/2013 (ኢዜአ) ሁሉም ኢትዮጵያዊ አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አስገነዘበ።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በሰላም፣ አብሮነት፣ በብዝሃነትና በግጭት አፈታት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአርባ ምንጭ ከተማ እየመከረ ነው።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በወቅቱ እንደገለጹት በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ ግጭቶችን ማስቆም ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ኅላፊነት ነው።  

"በሀገራችን በተለያዩ አከባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶችን በመፍታት አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል" ብለዋል።

በተለይም የሀይማኖት ተቋማት የሚፈጠሩ ግጭቶችን የመፍታትና ሰላምን የማስፈን  ትልቅ ኅላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

"ይሁንና ሰላም በሀይማኖት ተቋማት ብቻ የሚመጣ አይደለም " ያሉት ቀሲስ ታጋይ መላው ኢትዮጵያዊ በተናጠልና በጋራ መስራት ለሰላም መስፈን ኅላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዘበዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀን በሚቆየው የምክክር መድረክ የሀይማኖት ተቋማት ግጭት በሚፈጠርባቸው አካባቢዎች ሰላም ማውረድ በሚችሉባቸው አማራጮች ዙሪያ ውይይት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

በመድረኩ በግጭት አፈታት፣ በእምነትና ብሄር ብዝሀነት ዙሪያ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው በመርሀ ግብሩ ተመልክቷል።

በምክክር መድረኩ ከጋሞ፣ ጎፋና ኮንሶ ዞኖች እንዲሁም ከአሌ ልዩ ወረዳ የተውጣጡ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም