በምስራቅ ሸዋ ዞን በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት የተገነባው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመረቀ

81

አዲስ አበባ ጥር 3/2013 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በ20 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው 'ኢፈ ሊበን' ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመረቀ።

በምርቃት ስነ ስርዓቱ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶና ሌሎችም የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሊበን ጩቋላ ወረዳ ጎንጎ ቀበሌ ለምረቃ የበቃው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ አንድ ዓመት የወሰደ ሲሆን በዚህ ዓመት 220 ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ይጀምራል።

በክልሉ የዛሬውን ጨምሮ በሰሜን ሸዋ፣ በምዕራብ ሐረርጌና በምዕራብ ጉጂ ዞኖች በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ወጪ የተገነቡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ወደ ስራ ገብተዋል።

በተጨማሪም በተያዘው ዓመት በክልሉ ምዕራብ አርሲ፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ምዕራብ ወለጋና ጅማ ዞኖች በጽህፈት ቤቱ አማካኝነት ትምህርት ቤቶች እንደሚገነቡ ታውቋል።

በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት የሚገነቡ ትምህርት ቤቶች ረጅም ርቀት ተጉዘው የሚማሩ ተማሪዎች በአቅራቢያቸው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የማስቻልና የትምህርት ተደራሽነት የማስፋት ዓላማ ያላቸው ናቸው።

በተጨማሪም ጽህፈት ቤቱ ትምህርት ቤቶች በሌሉባቸው አካባቢዎች ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ለአካባቢው ማኅበረሰብ እያስረከበ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም