ቀጥታ፡

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በልማት ላይ ያላትን አስተዋፅኦ እንድታጠናክር ተጠየቀ

አዲስ አበባ ሀምሌ16/2010 የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለሰላምና ለአንድነት መረጋገጥ ከምታደርገው አስተዋፅኦ በተጨማሪ በልማት ስራዎች ላይ ያላትን ተሳትፎ አጠናክራ እንድትቀጥል የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ጠየቁ። ፕሬዚዳንቱ ይህን ያሉት 19ኛው የምስራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ህብረት መጠናቀቁን ተከትሎ በቤተመንግስት ባደረጉላቸው የእራት ግብዣ ላይ ነው። 19ኛው የምስራቅ አፍሪካ ካቶሊክ ህብረት ጉባኤ በኢትዮጵያ ከሐምሌ 6 ቀን 2010 ዓ ም ጀምሮ ''በእግዚአብሔር ላይ የተመሰረተ ሕያው ብዝኃነት፣ ሰብዓዊ ክብርና ሰላማዊ አንድነት ለምስራቅ አፍሪካ አገራት' በሚል መሪ ሀሳብ  ሲካሄድ ቆይቷል። ፕሬዚዳንት ሙላቱ ጉባኤው መጠናቀቁን ተከትሎ ለተሳታፊዎቹ ባደረጉት የእራት ግብዣ ላይ ቤተክርስቲያኗ ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት መረጋገጥ በፀሎትና በተለያዩ ተሳትፎዎች ዘርፈ ብዙ አስተዋፅኦ ስታደርግ መቆየቷን አስታውሰዋል። ''ሰላምና አንድነትን ያለኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ አይቻልም'' ያሉት ፕሬዚዳንቱ በዚህ ረገድ ቤተክርስቲያኗ በልማቱ ላይ ያላትን ያልተቋረጠ ተሳትፎ አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል።  የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በመላው አገሪቱ በሚሰሩ ማህበራዊና የልማት ስራዎች ላይ ድጋፍ ስታደርግ የቆየችና እያደረገች ያለችም መሆኑን ገልፀው በተለይ ጠንካራ የትምህርት ተቋማትን ከመመስረት አንፃር የተሰራውን ስራ አድንቀዋል። በአገሪቱ በተለያየ ጊዜ ለተከሰቱ አደጋዎች ድጋፍ ከማድረግ ጀምሮ የበጎ አድርጎት ስራዎችና የድህነት ቅነሳ ፕሮግራሞች ላይ እየሰራች መሆኗንም አስታውቀዋል። ''ጉባኤውን የተለየ የሚያደርገው ከአባል አገሮቹ ውስጥ ከምትገኘው ኤርትራ ጋር ሰላም በወረደበትና ወደቀድሞ አንድነት በተመለስንበት ወቅት መሆኑ ነው'' ብለዋል። 19ኛው የካቶሊክ ጳጳሳት ህብረት ጉባኤ ከሃምሌ 6 እስከ 15 ሲካሄድ የቆየ ሲሆን የጉባኤው ሊቀመንበር ኢትዮጵያዊው ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሊቀመንበርነታቸውን ለዛምቢያው ሊቀጳጳስ ቻርልስ ካሶንዴን አስረክበዋል። በጉባኤው ከአስራ አንድ የምስራቅ አፍሪካ አገሮች የተውጣጡ 400 የሚደርሱ ተሳታፊዎች የታደሙበት የነበረ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 150ዎቹ ጳጳሳት ናቸው። 20ኛው የምስራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት ጉባኤ በታንዛኒያ እንዲካሄድ ውሳኔ ተላልፏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም