ቀጥታ፡

የሴካፋ ሴቶች እግር ኳስ ውድድር ግንቦት 10 ይጀምራል

አዲስ አበባ ግንቦት 4/2010 በርዋንዳ አስተናጋጅነት ለ3ኛ ጊዜ የሚካሄደው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ ውድድር ግንቦት 10 ቀን 2010 ዓ ም ይጀመራል። 'ውድድሩ ከግንቦት 4 እስከ ግንቦት 14 ቀን 2010 ዓ.ም ይካሄል' ተብሎ የታቀደ ቢሆንም የርዋንዳ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሶስት ቀን በፊት ባወጣው መግለጫ አስፈላጊውን የፋይናንስ ድጋፍ ከሴካፋ ባለማግኘቱ ውድድሩን ማራዘሙን አስታውቆ ነበር። የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ የክለቦች ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) ርዋንዳ ላቀረበቸው ጥያቄ ሴካፋ ምላሽ በመስጠቱ ውድድሩ ከግንቦት 10 እስከ 20 ቀን 2010 ዓ.ም እንደሚካሄድ ታውቋል። በአሰልጣኝ ሰላም ዘርአይ የሚመራው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን 'ሉሲዎች' ለሴካፋ ውድድር ካለፈው ሳምንት ጀምሮ አዲስ አበባ ላይ ዝግጅት እያደረገ ሲሆን ግንቦት 9 ቀን 2010 ዓ.ም ወደ ርዋንዳ ያቀናል ተብሎ ይጠበቃል። አዘጋጇ ርዋንዳን ጨምሮ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ቡሩንዲ እና ጅቡቲ በሴካፋ ውድድር ላይ እንደሚሳተፉ ታውቋል። ከሁለት ዓመት በፊት ኡጋንዳ ውድድሩን ካስተናገደች በኋላ የሴካፋ የሴቶች እግር ኳስ ውድድር በበጀት ማጣት ምክንያት መዘግየቱ ይታወሳል። የሴካፋ ሴቶች እግር ኳስ ውድድር እ.አ.አ በ1986 ለመጀመሪያ ጊዜ ሲካሄድ ዛንዚባር ውድድሩን ያሸነፈች ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊት በኡጋንዳ በተካሄደው ውድድር ታንዛንያ አሸናፊ መሆኗ ይታወሳል። በኡጋንዳ በተካሄደው ውድድር የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሉሲዎች አዘጋጇ ኡጋንዳን አራት ለአንድ በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቃቸው ይታወሳል።
 
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም