በአንጎለላና ጠራ ወረዳ በአምስት ቢሊዮን ብር ወጪ የመስኖ ፕሮጀከት ግንባታ ተጀመረ

100

ደብረ ብርሃን፤ጥር 1/2013(ኢዜአ) በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን አንጎለላና ጠራ ወረዳ በአምስት ቢሊዮን ብር ወጪ ለሚካሄደው የአጅማ ጫጫ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ዛሬ መሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ ግንባታው ተጀመረ። 

የመስኖ ፕሮጀክቱን ግንባታ ያስጀመሩት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገርና የውሃ መስኖና ኢነርጅ ሚኒቴር ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ናቸው።

7ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት የሚያስችለውን የፕሮጀክት ግንባታ በቀጣይ ሦስት ዓመት አጠናቆ  ለአገልግሎት ለማብቃት መታቀዱም ተገልጿል።

የመስኖ ፕሮጀክቱ መገንባት በዞኑ ባሶና ወራና እና አንጎላላ ጠራ ወረዳዎች 10 ቀበሌዎች ውስጥ  የሚገኙ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የዞኑ መስኖ፣ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጅ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ደረጀ ማንደፍሮ አስታውቀዋል።

ግንባታው በአማራ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅትና በቻይና ሲቪል ኢንጅነሪንግ ግንባታ ኮርፖሬሽን (CCEC ) እንደሚከናወን ተመልክቷል።

በመስኖ ፕሮጀክቱ የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥና የግንባታ ማስጀመር ሥነ-ሥርዓት  የፌደራልና የክልል እንዲሁም የዞን ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም