በምዕራብ ወለጋ ዞን በመስኖ ልማት ከ23ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በዘር ተሸፈነ

52

ነቀምቴ፣  ጥር 1/2013(ኢዜአ) በምዕራብ ወለጋ ዞን በአንደኛው ዙር የመስኖ ልማት ከ23ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በዘር መሸፈኑን የዞኑ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ደሜ እንዳስታወቁት በዞኑ በበጋ ወራት በአንደኛው ዙር በመስኖ ይለማል ተብሎ በእቅድ የተያዘው 22ሺህ 552 ሄክታር መሬት ሙሉ በሙሉ በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑንና አፈፃፀሙም ከዕቅድ በላይ መሆኑን አስታውቀዋል ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም 1ሺህ 200 ሄክታር መሬት ለመጀመሪያ ጊዜ በስንዴ ዘር መሸፈኑን ያመለከቱት ሥራ አስኪያጁ፣ ከልማቱም 1ሚሊዮን 745ሺህ600 ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅም አመልክተዋል።

ከመደበኛ የእርሻ ሥራቸው በተጓዳኝ የመስኖ ልማትን በመጠቀም የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የውስጥ ገቢያቸውን ለማሳደግ እንደሚሰሩም ኢዜአ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች ተናግረዋል።

በገንጂ ወረዳ የብቅልቱ ኦንኮሪ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዋቅጅራ ተረፈ በሰጡት አስተያየት ከመደበኛ የእርሻ ሥራቸው በተጓዳኝ የመስኖ ልማትን በማካሄድ የውስጥ ገቢያቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በአንደኛው ዙር የመስኖ ልማት 1 ሄክታር መሬት ስንዴ፣ ግማሽ ሄክታር መሬት ደግሞ ላይ ደግሞ ድንች ማልማታቸውን ገልጸዋል።

የገንጂ 01 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ፍቅሩ በዳሣ በበኩላቸው ግማሽ ሄክታር መሬት በስንዴ ግማሽ ሄክታር መሬት ደግሞ በድንች መሸፈናቸውን አስረድተዋል።

የመስኖ ግብርና ቀደም ሲል ብዙም ያልተለመደ መሆኑን ገልጸው በቀጣይ ይሄንኑ አጠናክረው በመቀጠል የተሻለ ገቢ ለማግኘት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

የቡሳኖ ሰጤ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አስፋው ከበደ በበኩላቸው 1 ነጥብ 5 ሄክታር መሬታቸው ላይ ከመኸር ግብርና በኋላ መስኖን በመጠቀም የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በማልማት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ከነዚህ መካከልም ድንች፣ ጥቅል ጎመን፣ ካሮትና ቀይ ስር የመሳሰሉትን በማልማት ዓመታዊ ገቢያቸውን ለማሳደግ በሚያስችል ሁኔታ ላይ እንደሚገኙም አመልክተዋል።

በዚህ ዓመት በዞኑ በመስኖ ለማልማት ከታቀደው 22ሺህ 552 ሄክታር መሬት በተጨማሪ 1ሺህ 200 ሄክታር መሬት ለመጀመሪያ ጊዜ በስንዴ ልማት መሸፈኑም ከዞኑ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም