በታሪክ ላይ ትክክለኛውን ነገር መያዝ ለምናደርገው የዘላቂ ሰላም ግንባታ ፋይዳው የጎላ ነው - የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

78

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 30/2013 ( ኢዜአ) በታሪክ ላይ ትክክለኛውን ነገር መያዝ ለምናደርገው የዘላቂ ሰላም ግንባታ ፋይዳው የጎላ ነው ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ተናገሩ።

በሰላም ሚኒስቴር አዘጋጅነት “የሰላም ወግ፤ ብሔራዊ መግባባት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል ባደረጉት ንግግር “የሰላም ወግ” በአገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄዱ ካሉ መድረኮች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

መድረኩ አገራዊ መግባባት ለማምጣት የተዛቡ አስተሳሰቦችን በትክክለኛው ቦታ ለማስቀመጥ ሁሉም የሚሳተፍበት እና በእውቀት ላይ መሰረት ያደረገ ውይይት የሚደረግበት መሆኑን ገልጸዋል።

በታሪክ ላይ ተገቢውን እሳቤ መያዝ ለሚደረገው  የዘላቂ ሰላም  ግንባታ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።

"በእውቀት ላይ ተመስርተን ለእውነት የተጠጉ ሃሳቦችን ለመያዝ  ተቀራርቦ መወያየትና መነጋገር ተገቢ ነው" ሲሉም ገልጸዋል።

የውይይት መድረኩ ከግል ስሜትና ከቡድን ፍላጎት በፀዳ መንገድ የጋራ ለሆነው የአገር ግንባታ ፋይዳ እንዳለውም ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዓለ ፈለገ ሰላም ሥነ ጥበብ ትምህርት መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌውን ጨምሮ የመቀለ ዩኒቨርሲቲ የቅርስ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር አየለ በከሪ እና የአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ዶክተር አልማው ክፍሌ የመነሻ ፅሁፍ አቅርበዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ጽሁፋቸው ለብሔራዊ መግባባትና አገር ግንባታ ታሪክ ጉልህ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ህብረ ብሄራዊ አገሮች ታሪክ በትክክለኛው መንገድ ከተነገረና ተሰንዶ ከተቀመጠ በህዝቦች መካከል ጠንካራ ትስስር ይፈጥራልም ብለዋል።

እያንዳንዱ አገር ታሪኩን እያስጠና የሚያስቀምጠው ትውልድን መገንቢያ ሀብት በመሆኑ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ዶክተር አልማው የአገሪቱ ታሪክ በትክክለኛው መንገድ ተፅፎና ተሰንዶ ባለመቀመጡ ታሪክን በተገቢው ሁኔታ እንዳንረዳ አድርጎናል ይላሉ።

የኢትዮጵያ ታሪክ  በብዛት የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት በመጡ የውጭ ተጓዦችና ሚሽነሪዎች በመጻፉ ግጭቶች  በየቦታው እንዲቀሰቀሱ  መነሻ መሆኑንም አብራርተዋል።

ሆኖም ታሪክ ትምህርት ቤት እንጂ፤ የግጭት መንስኤ አለመሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል።

ዶክተር አየለ በበኩላቸው “የሰው ልጅን በተዛባ ታሪክና በተፈበረከ ጥላቻ እምቅ ሀይሉን ተግባር ላይ ሳያውል በድንገትና በጭፍን መቅጠፍ የከፋ ወንጀል ነው” ብለዋል።

ልዩነቶችን በመግባባትና በውይይት ለመፍታት መሞከርና ለሰው ልጅ የሚገባውን ክብር መስጠት እንደሚገባም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም