ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሁከቱን አበረታተዋል በሚል ተቃውሞ ከሃላፊነት የለቀቁ ባለስልጣናት ቁጥር 10 ደረሰ

49

ታህሳስ 30/2013 ( ኢዜአ) የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ከ13 ቀናት በኋላ የነጩ ቤተ-መንግስት ስልጣናቸውን ለአዲሱ ተመራጭ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ለማስረከብ ዝግጅት እያደረጉ ባለበት በዚህ ወቅት 10 ሹማምንቶቻቸው ከሀላፊነት መልቀቃቸውን እያሳወቁ ነው፡፡

ረቡዕ ዕለት ፕሬዚደንት ትራምፕ በቲውተር ገጻቸው ላይ ያስተላለፉትን መልዕክት መሰረት በማድረግ ደጋፊዎቻቸው በዋና ከተማዋ ከፍተኛ ሁከት ቀስቅሰው እንደነበር የሚታወስ ነው።

ይህን ተከትሎ 10 ባለስልጣናት በፍቃዳቸው ከስልጣናቸው ለመነሳት መልቀቂያ ማስገባታቸውን ኤ ቢ ሲ ኒውስ ዘግቧል፡፡

ስልጣናቸውን ከለቀቁት ሀላፊዎች መካከል 5ቱ የነጩ ቤተ-መንግስት ሀላፊዎችና የፕሬዝዳንቱ የቅርብ ሰዎች ናቸው።

እነዚህም የብሔራዊ ደህንነት ምክትል አማካሪ ማቲው ፖቲንገር፣ የነጩ ቤተ-መንግስት ካውንስል የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተጠባባቂ አማካሪ ቴይለር ጉድስፒድ፣ የፕሬዚደንቱ ባለቤት ጽ/ቤት ሀላፊና ቃላ-አቀባይ የሆኑት ስቴፋኒ ግሪሻም፣ የነጩ ቤተ-መንግስት ማህበራዊ ጉዳይ ሀላፊ የሆኑት ሪኬይ ኒሲታ እንዲሁም የነጩ ቤተ-መንግስት ምክትል ቃል-አቀባይ የሆኑት ሳራህ ማቲው መሆናቸው ታውቋል።

ሌሎቹ ባለስልጣናትም ከሃላፊነታቸው ራሳቸውን ያገለሉ ሲሆን በዋና ምክንያትነት የተጠቀሰውም ፕሬዚደንቱ ረቡዕ ዕለት የተከሰተውን ሁከት ማበረታታቸውን በመቃወም መሆኑን በዘገባው ተመላክቷል፡፡

ከእነዚህ መካከልም የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ኢላይን ቻዎ፣ የሀገሪቱ የንግድ ደህንነትና መረጃ ቢሮ ምክትል ሀላፊ ጆን ኮስቴሎ፣ የቀድሞ የነጩ ቤተ-መንግስት ሀላፊ የነበሩትና አሁን ላይ በሰሜን አየርላንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ማይክ ሙልቫኒ ይገኙበታል።

በነጩ ቤተ-መንግስት የአውሮፓና ሩሲያ ጉዳዮች ከፍተኛ ሀላፊ የሆኑት ሪያን ቱሊይ እንዲሁም የሀገሪቱ የትምህርት ሚኒስትር የሆኑት ቤትሲ ዴቮስ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም