የምርት ብክነትን ለመቀነስ ዘመናዊ የሰብል መሰብሰቢያ ማሽን በብዛት ጥቅም ላይ እየዋለ ነው

54

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 30/2013 ( ኢዜአ) በሰብል አሰባሰብ ወቅት ምርት ብክነትን ለመቀነስ ዘመናዊ የሰብል መሰብሰቢያ ማሽነሪ በብዛት ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በዘንድሮው መኸር እስካሁን በ360 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማ ሰብል በኮምባይነር መሰብሰቡም ታውቋል። 

በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ለማ ለኢዜአ እንደተናገሩት የምርት ብክነትን ለመቀነስ የሰብል አሰባሰቡ በተቻለ መጠን በኮምባይነር እንዲሆን እየተሰራ ነው።

በኮምባይነር እንዲሰበሰብ ከማድረግ በተጨማሪም ለአርሶ አደሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል።

በዘንድሮው መኸር እስካሁን ከ360 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማ ሰብል በኮምባይነር መሰብሰቡንም ገልጸዋል።

የምርት ብክነትን ለመቀነስ ሲባል አሰራርን የማዘመን ሥራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አክለዋል።

ከዚህ በፊት በተወሰኑ የአገሪቱ አካባቢዎች ብቻ የነበረውን የኮምባይነር አቅርቦት የማሻሻል ስራም መከናወኑን አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት በብዙ የአርሶ አደር ማህበራትና ዩኒየኖች አማካኝነት ኮምባይነሮች ከቀረጥ ነጻ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጉንም ተናግረዋል።

በአማራ፣ በኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች እስካሁን ከ360 ሺህ ሄክታር በላይ የደረሰ ሰብል በኮምባይነር መሰብሰቡን የገለጹት ዳይሬክተሩ በቀጣይ ሶማሌ ክልልን ጨምሮ ከግማሽ ሚሊዮን ሄክታር በላይ ሰብል ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ምርት ከተሰበሰበ በኋላ  በጎተራ ብልሽት እንዳይገጥመው የማፅዳት፣ ፕላስቲክ ያለው ማዳበሪያ መጠቀም እና በአይጥና ነብሳት እንዳይበላ ጥንቃቄ እንዲደረግ እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት።

የብረት ጎተራና የፕላስቲክ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እየቀረበ ነው ብለዋል ዳይሬክተሩ።

በምርት አሰባሰብና ማስቀመጥ ወቅት በስንዴ ምርት ላይ የብክነት መጠኑ አነስተኛ ቢሆንም ማሽላና በቆሎ በነቀዝ የመበላት እድላቸው ከፍተኛ መሆኑ ይነገራል።

በመሆኑም የምርት ብክነት የማይታይ ጉዳት መሆኑን አርሶ አደሩ ተገንዝቦ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ ከሚመረተው ዓመታዊ የሰብል ምርት በአማካይ ከ25 በመቶ በተለያየ አጋጣሚ እንደሚባክን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም