ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በከተማዋ ከተፈጠረው ቀውስ በኋላ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንደሚያደርጉ ቃል ገቡ

67

ታህሳስ 30/2013 (ኢዜአ) የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎቻቸው ከፈጠሩት ነውጥ በኋላ በሰጡት መግለጫ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንደሚያደርጉ ገለጹ።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሁን ላይ ትኩረታቸው የስልጣን ሽግግሩ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚተላለፍበት ጉዳይ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጆ ባይደን ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ስለመሆናቸው ዕውቅና እንደሚሰጡ ማስታወቃቸውን አልጀዚራ በዘገባውአስነብቧል፡፡

ፕሬዚደንቱ አክለውም የስልጣን ሽግግሩ ሰላማዊ፣ ህጋዊና ከሁከት በጸዳ መንገድ እንዲከናወን ማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

አወዛጋቢው የአሜሪካ መሪ በተፈጠረው ችግር ዙሪያ በመነጋገር የእርቅ መንገድ የምናፈላለግበት ወቅት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ፕሬዚደንት ትራምፕ በከተማዋ የተከሰተው ቀውስ ''የአሜሪካንን የዲሞክራሲ ታሪክ የሚያጠለሽ''ሲሉ አውግዘዋል፡፡

በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት ፕሬዚደንቱ ከራሳቸው ከሪፐብሊካን አባላትና አመራሮች ፓርቲ ጠንካራ ትችቶች ደርሶባቸዋል።

የዲሞክራት ፓርቲ አመራሮች ደግሞ ግጭቱ እንዲቀሰቀስ አነሳስተዋል በሚል ከስልጣናቸው በአስቸኳይ እንዲለቁ ጥሪ እያቀረቡ ነው።

ይህ ሁሉ ቀውስ እየተፈጠረ ያለው ላለፉት በርካታ ወራት የምርጫውን ውጤት በተመለከተ ፕሬዚደንቱ ምንም አይነት ማስረጃ ሳይኖራቸው ምርጫው ተጭበርብሯል የሚል ትችት ሲያሰራጩ በመቆየታቸውና ለደጋፊዎቻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ምክንያት መሆኑንም ተገልጿል።

አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ከ12 ቀናት በኋላ ጃኑዋሪ 20 ስልጣን በይፋ እንደሚረከብ ዘገባው አስታውሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም