በቄለም ወለጋ ዞን የበጋው ወራት የተፋሰስ ልማት ሥራ ተጀመረ

64

ነቀምቴ፣ ታሕሳስ 30/2013 (ኢዜአ ) በቄለም ወለጋ ዞን ለ45 ቀናት የሚቆይ የበጋው ወራት የተፋሰስ ልማት ሥራ መጀመሩን የዞኑ የእርሻ እና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ተወካይ አቶ ጀቤሣ ደገፋ እንደገለጹት የልማት ሥራው የተጀመረው በዞኑ ሰዲ ጫንቃ ወረዳ ውስጥ ነው፡፡

የዘንድሮው በጋ ወራት  በዞኑ በሚገኙ 12 ወረዳዎች   በተመረጡ 266 ተፋሰሶች ውስጥ 117 ሺህ 366 ሄክታር መሬት የሚሸፍን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እንደሚካሄድ አመልክተዋል፡፡


እንዲሁም  11 ሺህ 957 ሄክታር መሬትም ከሰውና እንሳስት ንክኪ የመከለል ሥራ እንዳለም አስረድተዋል፡፡

በዞኑ ህብረተሰብ ተሳትፎ በሚካሄደው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የሥነ ሕይወታዊ ሥራዎችን ለማጠናከር ችግኞችን በተመረጡ ተፋሰሶች ውስጥ ለመትከልም  ዝግጅቱ  መቀጠሉን  አቶ ጀቤሣ ተናግረዋል፡፡

የሰዲ ጫንቃ ወረዳ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጫሊ ተርፋሳ በበኩላቸው  የዘመኑ የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራው በወረዳው በተለዩ 13 ተፋሰሶች ውስጥ 7 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ ለማካሄድ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ እንዳሉት በወረዳው 803 ሄክታር መሬት ከሰውና እንስሳት ንክኪ የመከለልና  እርከን ሥራም ይካሄዳል።

በቄለም ወለጋ ዞን ቀድሞ የተጀመረው የበጋ ወራት የተፋሰስ ልማት ሥራ  በአሮሚያ ክልል ደረጃ  ከጥር1/2013ዓ.ም አንስቶ እንደሚቀጥል ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም