በሐረር ከተማ የእርድ እንስሳት ዋጋ የተረጋጋ መሆ ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
በሐረር ከተማ የእርድ እንስሳት ዋጋ የተረጋጋ መሆ ተገለፀ
ሐረር ታህሳስ 28 ቀን 2013( ኢዜአ) በሐረር ከተማ በገና በዓል ዋዜማ በዋለው ገበያ የእርድ እንስሳት ዋጋ ቅናሽ መታየቱን ሻጭና ሸማቾች ተናገሩ።
በሐረር ጀላባ የእርድ እንስሳት ንግድ የተሰማሩ አቶ ሞገስ መንግስቱ ለኢዜአ እንዳሉት በዘመን መለዋጫ በዓል እስከ 45 ሺ ብር ይሸጥ የነበረው ትልቅ ሰንጋ እስከ 35 ሺህ ብር ፣ መካከለኛ 30ሺሃ እና 25ሺ ብር ይሸጥ የነበረው አሁን በ10ሺህ ብር ያህል ቀንሷል።
ባለፈው በዓል እስከ 5ሺህ ይሸጡ የነበሩት ሙክት ፍየሎች አሁን እስከ 3ሺ 700 ብር፣ወጠጤ ፍየል ደግሞ 2ሺ እና 1ሺ 800 ብር በመሸጥ ከ300 እስከ 400 ብር የዋጋ ቅናሽ አሳይቷል ያሉት ደግሞ በዚህ ንግድ የተሰማሩት አቶ እንዳለ ማሞ ናቸው።
የእርድ እንስሳት ሲገዙ የነበሩት አቶ ግርማ ይበቃል በበኩላቸው የከብት ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ቅናሽ አሳይቷል፤እንደ ፍላጎታችንና አቅማችን አግኝተናል ብለዋል።
ለዋጋው መቀነስም የእርድ እንስሳት በብዛት ወደ ገበያ በመቅረቡ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
በከተማው ሸዋበር የገበያ ስፍራ በዶሮ ንግድ የተሰማራችው ወጣት ቢንሲቱ አብዲ በሰጠችው አስተያየት የስጋ ዶሮ ትልቁ 200 ብር እና መካከለኛ 150 ብር እየሸጥን ነው ብላለች።
ከዘመን መለወጫ በዓል ጋር ሲነጻጸር በ50 ብር ቅናሽ ማሳየቱን ገልጸው አንድ እንቁላል ስድስት ብር እንደሚሸጥ ተናግራለች።
አንድ ኪሎ የቀላፎ ሽንኩርት 30 ብር፣ቲማቲም 25 ብር በመሸጥ ካለፈው ሳምንታት የአምስት ብር ጭማሪ ሲያሳይ ፤ነጭ ሽንኩርት በኪሎ 80 ብር እንዲሁም ዝንጅብል 40 ብር በመሸጥ የዋጋ ለውጥ አላሳየም።
ኪሎ ለጋ ቅቤ 300 ብር እንዲሁም የተዘጋጀ ኪሎው በርበሬ በ200 ብር በመሸጥ የዋጋ ልዩነት እንደሌለው የተናገረችው ወይዘሪት ሃና ሙሉጌታ ናት።
ዘይት በከተማው በመጥፋቱ አምስት ሊትር ዘይት 410 ብር ለመግዛት ተገደናል፤ ይህም ቀደም ሲል ከነበረው 70 ብር ጭማሪ አሳይታል ብላለች።