የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ህብረተሰቡ የብር ኖቶችን በጥንቃቄ እንዲጠቀምባቸው አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ህብረተሰቡ የብር ኖቶችን በጥንቃቄ እንዲጠቀምባቸው አሳሰበ
አዲስ አበባ ታህሳስ 28/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ህብረተሰቡ የብር ኖቶችን በጥንቃቄ እንዲጠቀምባቸው አሳሰበ። ''የተጻፈበትን ብር አትቀበሉ" ተብሎ የሚናፈሰው ወሬም መሰረተ ቢስ መሆኑን አስታውቋል።
በብር ኖቶች ላይ መጻፍና በተለያዩ መልኮች ማበላሸት በሕግ እንደሚያስጠይቅ አስታውቋል።
ባንኩ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ''የብር ኖቶች በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የሚታተም የሕዝብ ሐብት በመሆኑ በጥንቃቄ ተይዞ ሕብረተሰቡ ለረጅም ጊዜ ሊገለገልበት ይገባል'' ብሏል።
በመሆኑም ህብረተሰቡ የብር ኖቶችን በጥንቃቄ ሊጠቀምባቸው እነደሚገባ አሳስቧል።
የተጻፈባቸው የብር ኖቶች ተቀባይነት እንደሌላቸው ተደርጎ የሚሰራጨው ወሬም የተሳሳተ ስለመሆኑ ገልጿል።
ሆኖም የብር ኖቶቹ ላይ ''መጻፍ፣ መቅደድና በቀለም ማበላሸት፣ የትኛውንም አይነት ጉዳት ማድረስና ምልክቶቹን ያለ ፈቃድ ማባዛት የተከለከለና በሕግ እንደሚያስጠይቅ'' አስታውቋል።
''በጣም የተጎዱ የብር ኖቶች ሲያጋጥሙ ከዝውውር ስለሚወጡበት ሁኔታ ዝርዝር መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑንም'' አመልክቷል።
በተጨማሪም በኖቶቹ አጠቃቀም ላይ በየጊዜው ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ እንደሚያስጨብጥ ገልጿል።
ባንኩ አዲስ የብር ኖቶችን አሳትሞ ከመስከረም 6 እስከ ታህሳስ 6 ቀን 2013 ዓ.ም መቀየሩ ይታወቃል።