ቀጥታ፡

ፖሊስ የህዝብን ሠላምና ደህንነት የማስጠበቅ ኅላፊነቱን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - አቶ ደስታ ሌዳሞ

ሀዋሳ ታህሳስ 28/2013 (ኢዜአ)- የሲዳማ ክልል ፖሊስ የህዝብን ሠላምና ደህንነት ለመጠበቅ እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስገነዘቡ ፡፡

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች የገና በዓልን ከክልሉ የፀጥታ አካላት ጋር በተለያዩ ስነ ስርአቶች አክብረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በሀዋሳ የሚገኙ የክልሉ አድማ ብተናና ልዩ ኃይል ፖሊስ ጊዜያዊ ካምፖችን የጎበኙ ሲሆን በሲዳማ ባህል አዳራሽ በነበረው የገና በዓል አከባበር ሰነ ስርአት ላይ ተገኘተው የእንኳን አደረሳችሁና የሥራ መመሪያ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል፡፡

የክልሉ አድማ ብተና ልዩ ኃይል ፖሊስ ከተደራጀ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ በመግባት ከሀገር መከላከያ፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከመደበኛ የፖሊስ ኃይል ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

"በተሰራው ስራ ሰላም ማስከበር በመቻሉ የክልሉ ዋና ከተማ ሀዋሳ ቀድሞ ወደ ምትታወቅበት የቱሪስት መናኸሪያነት ተመልሳለች " ብለዋል።

ሰላም መሰፈኑን ተከትሎም በርካታ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ ክልሉ እየመጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

"ሠላማችንን አጠናክረን በማስቀጥል የህዝባችንን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይኖርብናል" ብለዋል።

የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት ባልተመቸ ሁኔታ ውስጥ  ሆነው በህዝብና በመንግስት የተሰጣቸውን ተልዕኮ ሲወጡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

የክልሉ መንግስት አቅም በፈቀደ መልኩ የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ማሻሻያ ለማድረግ  እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ በበኩላቸው "ሲዳማ ክልል ሆኖ ሲደራጅ የትርምስ ቀጠና ይሆናል በሚል የተሳሳተ ግምት አሉታዊ አስተያየቶች ከየአቅጣጫው ሲሰነዘሩ ቆይተዋል" ብለዋል።

"ሁላችንም አንድ ሆነን በመሥራታችን የክልሉ ሠላም ይበልጥ ተጠብቆ እንዲቀጥል እንዲሁም በውስጡ የሚገኙ የሁሉም ብሔር ተወላጆች እንደቀድሞው ደህነታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ ማድረግ ተችሏል" ሲሉም ተናግረዋል።

ሲዳማ አሁን ያለው ዋንኛ ጥያቄው ልማትና መልካም አስተዳደር መሆኑን የገለጹት ኅላፊው  "ጥያቄዎቹን መመለስ የሚቻለው  ሠላምን የመጀመረያ አጀንዳችን  አድርገን ስንሰራ ነው" ብለዋል፡፡

የክልሉ ፖሊስ አባላት በህዝብ ዘንድ እያገኙ ያሉትን ተአማኒነት አጠናክረው ማስቀጠል እንደሚጠበቅባቸው እስገንዘበዋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አበራ አሬራ በበኩላቸው በሀገር ደረጃ የመጣውን ለውጥ ለማደናቀፍና ሀገሪቱን ለመከፋፈል የሚጥሩ የህወሀት ጁንታና የኦነግ ሸኔ ቡድኖች ሲዳማንም የትርምስ ማዕከል ለማድረግ ዝግጅት አድርገው ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

የፀጥታ ኃይሉ ሁኔታውን ነቅቶ በመጠበቅ ክልሉ የሠላም ቀጠና ሆኖ እንዲቀጥል ብርቱ ጥረት ማድረጉን አመልክተዋል፡፡

"ርዕሰ መስተዳድሩ የገናን በዓል ከኛ ጋር አብረው ለማሳለፍ በመካከላችን መገኘታቸው የሚያስደስትና ለበለጠ ሥራ የሚያነሳሳን ነው" ያሉት ደግሞ የክልሉ አድማ ብተናና ልዩ ኃይል አባል ምክትል ኢንስፔክተር ኢያሱ ተስፋዬ  ናቸው።

"ፖሊስ ከራሱ በፊት ለህዝብና ለሀገር ቅድሚያ በመስጠት የሚሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ የሚፈፅም ኃይል ነው " ብለዋል።

ለወደፊትም ፖሊሳዊ ሥነ ምግባርን በመጠበቅ የህዝቡን ደህንነትና ሠላም የማስጠበቅ ተልዕኳቸውን እንደሚወጡ አመላክተዋል፡፡

በበዓል ዝግጅቱ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የፀጥታ ዘርፍ አመራር አባላት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም