የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይ መፍትሔ የሚያገኘው ሁለቱ ሀገራት የጋራ መግባባት ላይ ሲደርሱ ብቻ ነው... አምባሳደር ኢብራሂም እድሪስ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይ መፍትሔ የሚያገኘው ሁለቱ ሀገራት የጋራ መግባባት ላይ ሲደርሱ ብቻ ነው... አምባሳደር ኢብራሂም እድሪስ
አዲስ አበባ ታህሳስ 28/2013 (ኢዜአ) በዳግላሽ ተራራ በስተሰሜን ያለው የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይ መፍትሄ ማግኘት የሚችለው ሁለቱ ሀገሮች የጋራ መግባባት ላይ ሲደርሱ ብቻ እንደሆነ የኢትዮ-ሱዳን የጋራ ድንበር ኮሚሽን አባል አምባሳደር ኢብራሂም እድሪስ ገለጹ።
የኢትዮ-ሱዳን የጋራ ድንበር ኮሚሽን አባላት በኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ጉዳይ ዙሪያ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
የኮሚሽኑ አባል አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ የኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ማካለል ጉዳይ መፍትሔ ለመስጠት የተጀመረው ስራ 118 ዓመት ማስቆጠሩን ገልጸዋል።
እ.አ.አ በ1902 እና 1907 የድንበሩን ጉዳይ አስመልክቶ ስምምነቶች መፈረማቸውንና በ1902 ስምምነት መሰረት ጉዊን የሚባል እንግሊዛዊ የመሬት ቀያሽ(ሰርቬየር) የድንበር ማካለል ስራ ማከናወኑን ተናግረዋል።
ነገር ግን የድንበር ማካለሉ የተካሄደው ያለ ኢትዮጵያ መንግስት እውቅና በመሆኑና በሌሎች ምክንያቶች የኢትዮጵያ መንግስት የጉዊንን የድንበር ማካለል ሪፖርት አለመቀበሉን አስታውሰዋል።
ከዛም በኋላ ባሉ ጊዜያት ድንበርን በሚመለከት በተደጋጋሚ አለመግባባቶች በመከሰታቸው ምክንያት ሁለቱ ሀገሮች እ.አ.አ 1972 የማስታወሻ ለውጥ ስምምነት(Exchange of notes) በመፈራረም የጋራ ድንበራቸውን እንደገና ለማካለል መስማማታቸውን ነው አምባሳደር ኢብራሂም ያስረዱት።
በዚሁ መሰረት ከዳግላሽ ተራራ በስተሰሜን ባለው የድንበር ክፍል ውስጥ ከእርሻና ከሰፈራ ጋር በተያያዘ የሚነሳው ጥያቄ በሁለቱ አገራት መካከል ተቀባይነት ያለው መፍትሄ እስኪቀርብ ድረስ ነባራዊ ሁኔታው ተከብሮ እንዲቆይ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።
በስምምነቱ መሰረት በሁለቱ አገራት ተቀባይነት ያለው የመፍትሔ ሀሳብ ላይ ሲደረስ የጋራ ድንበር እንደገና ይካለላል የሚል ሀሳብ መያዙን ገልጸው፤ ለዚህም የጋራ ልዩ ኮሚቴ ተዋቅሯል ብለዋል።
ሱዳን ስምምነቱን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር አንቀጽ 102 መሰረት እንዲመዘገብ ከፍተኛ ጥረት ስታደረግ እንደነበረም ነው አምባሳደሩ ያብራሩት።
እ.አ.አ በ2002 በሱዳና መዲና ካርቱም በተካሄደ ስብሰባ ሁለቱ አገራት የጋራ ድንበር ኮሚሽን፣የጋራ ድንበር ቴክኒክ ኮሚቴና የጋራ ልዩ ኮሚቴ ማቋቋማቸውን አስታውሰዋል።
የጋራ ድንበር ኮሚሽኑ፣ የጋራ ድንበር ቴክኒክ ኮሚቴና የጋራ ልዩ ኮሚቴ የሚያቀርቧቸውን ሪፖርቶች በመገምገም መመሪያዎች ሲሰጥና ለሁለቱ አገር መንግስታት ሲያቀርብ መቆየቱንም አንስተዋል።
የቴክኒክ ኮሚቴው ድንበሩን እንደገና ለማካለል አስፈላጊ የሆኑትን የቅድመ ቅየሳ ስራና ድንበሩን ለማካለል የሚያስፈልገውን በጀት ማዘጋጀቱንም ገልጸዋል።
የጋራ ልዩ ኮሚቴው ደግሞ እ.አ.አ በ1972 በተፈረመው የማስታወሻ ስምምነት መሰረት በሁለቱ አገሮች ተቀባይነት የሚኖረው የውሳኔ ሀሳብ ለመቅረብ ስብሰባዎችን መካሄዱንም ተናግረዋል።
ነገር ግን ልዩ ኮሚቴው የመጨረሻ ሪፖርቱን እንዳላቀረበ አስረድተዋል።
ይህ ባለበት ሁኔታ የሱዳን ጦር በዳግላሽ ተራራ በስተሰሜን ያለውን አካባቢ ጥሶ መግባቱን ነው አምባሳደር ኢብራሂም ያመለከቱት።
በድርጊቱም በርካታ አርሶ አደሮች ከቀያቸው መፈናቀላቸውንና የግብርና ምርቶችና መሳሪያዎች መውደማቸውን ጠቁመዋል።
ሱዳን የፈጸመችው ድርጊትም እ.አ.አ በ1972 የተፈረመውን ስምምነትን የጣሰ መሆኑን ጠቅሰው፤ ድርጊቱም ሱዳንን በሕግ እንደሚያስጠይቃት ተናግረዋል።
በመሆኑም ሱዳን ለፈረመችው ስምምነት ተገዢ መሆን አለባት ብለዋል።
ሱዳን ስምምነቱን የጣሰችው የጋራ ልዩ ኮሚቴው በሁለቱ አገራት ተቀባይነት ያለው የመጨረሻ የመፍትሔ ባለቀረበበት ሁኔታ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዳግላሽ ተራራ በስተሰሜን ያለው ድንበር እንደገና ሊካለል የሚችለው ኢትዮጵያና ሱዳን የጋራ መፍትሔ ላይ ሲደርሱ ብቻ መሆኑንም ነው አምባሳደሩ የተናገሩት።
በመሆኑም ሱዳን በሕገ-ወጥ መንገድ የያዘችውን መሬት ለቃ መውጣት እንዳለባት አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ ጉዳዩ በድርድርና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ አስፈላጊውን ጥረት እንደምታደረግም ነው አምባሳር ኢብራሂም ያስረዱት።
የኢትዮጵያና ሱዳን ሕዝቦች ረጅም ዘመናት የቆየ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ያስታወሱት አምባሳደር ኢብራሂም፤ሱዳን የፈጸመችው ድርጊት ከወዳጅ አገር የማይጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላኛው የኢትዮ-ሱዳን የጋራ ድንበር ኮሚሽን አባል አቶ ውሂብ ሙሉነህ በበኩላቸው ዓለም አቀፍ ተሞክሮ የሚያሳየው የድንበር ማካለል ጉዳዮች መፍትሔ የሚያገኙት በድርድርና በውይይታ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና ሱዳን የጋራ ድንበር ኮሚሽን፣ የጋራ ድንበር ቴክኒክ ኮሚቴና የጋራ ልዩ ኮሚቴ መዋቅሮቻቸውን ተጠቅመው ለጉዳዩ እልባት ማበጀት እንደሚጠብቅባቸውም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያና ሱዳን ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴ ጉዳዩን በሚለከት ከታህሳስ 13 እና 14 ቀን 2013 ዓ.ም በካርቱም የተወያዩ ሲሆን፤ቀጣይ ስብሰባውን በአዲስ አበባ ለማድረግ ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወሳል።