ቀጥታ፡

በነጃሺ መስጅድና መካነ ቅርስ ላይ የደረሰውን ጥቃት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አወገዘ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 28 ቀን 2013 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል በሚገኘው ታላቁ ነጃሺ መስጅድና ታሪካዊ መካነ ቅርስ ላይ የደረሰውን ጥቃት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በፅኑ አወገዘ፡፡

ጠቅላይ ምክር ቤቱ ቅርሱ የደረሰበትን የጉዳት መጠን የሚያጣራ ቡድን ወደ ስፍራው ለመላክ መዘጋጀቱንም ገልጿል።

የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፀሃፊ ሼህ ቃሲም መሃመድ ታጁዲን በሰጡት መግለጫ "ነጃሺ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ቅርስ ነው" ብለዋል።

ነጃሺ በዓለም የመጀመሪያው የስደተኞች መብትና ሰዎች የፈለጉትን እምነት በነጻነት እንዲያራምዱ በንጉስ ነጃሺ የተፈቀደበት ታሪካዊ ቦታ መሆኑንም አብራርተዋል።

ቦታው የታላቁ ንጉስ ነጃሺ እና ሌሎች የነብዩ ሙሃመድ ባልደረቦች መካነ መቃብር ስፍራና በእለም ከሚገኙ ጥቂት ጥንታዊ መስጅዶች አንዱና ታሪካዊ ስፍራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመሆኑም በታላቁ ነጃሺ መስጅድና የመካነ መቃብር ቅርስ ላይ በደረሰው ጥቃት ጠቅላይ ምክር ቤቱ ማዘኑን ገልጸዋል።

በመስጅዱና ቅርሱ ላይ የተፈፀመው ጥቃት ኢትዮጵያዊያንን ብቻ ሳይሆን የዓለም ሙስሊሞችንም ያሳዘነ ድርጊት መሆኑን ገልጸዋል።  

የሶሪያን ስደተኞች ጀርመን ስትቀበል መራሂተ መንግስት አንጌላ መርክል ‘’እንደ ኢትዮጵያ ንጉስ ነጃሺ ስደተኞችን በተቸገሩና መሄጃ ባጡ ጊዜ እንዳስጠለለው እኛም ተቀብለን እናስተናግዳለን’’ ማለታቸውን ሼህ ቃሲም በመግለጫው በማስታወስ የንጉስ ነጃሺን ታላቅነት አንስተዋል።

ምክር ቤቱ በመስጅዱና ታሪካዊ መካነ ቅርሱ ላይ የደረሰውን ጉዳት ትክክለኛ መረጃ እና ማብራሪያ እንዲሰጠው ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡  

ጠቅላይ ምክር ቤቱ ቅርሱ የደረሰበትን የጉዳት መጠን የሚያጣራ ቡድን ወደ ስፍራው በመላክ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡  

ለመስጅዱ ጥገና ለማድረግ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።

መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ለታሪካዊ ቦታዎች እና ቅርሶች ተገቢውን ትኩረትና ልዩ ጥበቃ እንዲያደርግም ምክር ቤቱ አሳስቧል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም