ቀጥታ፡

ሕዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር ለሰው ልጆች አክብሮትና ፍቅር በመስጠት ሊሆን ይገባል- የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ

አዲስ አበባ ታህሳስ 28/2013 (ኢዜአ) ሕዝበ ክርስቲያኑ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል (ገና) ሲያከብር ለሰው ልጆች አክብሮትና ፍቅር በመስጠት እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሰላም በጋራ በመቆም ሊሆን እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለገና በአል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

የገና በዓል ለሰው ልጆች ሲባል የተከፈለን ዋጋ የሚያሳይ በመሆኑ ሕዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር ይህንኑ ዋጋ በማስታወስ ለሰው ልጆች አክብሮትና ፍቅር በመስጠት ሊሆን እንደሚገባ ጉባኤው ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ሕዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር በኢትዮጵያ አሁን ያለው የሰላም ችግር በዘላቂነት እንዲፈታ ፀሎት በማድረግ እንዲሁም ለሰላም የሚደረጉ ማንኛውንም ጥረቶች በማገዝ ሊሆን ይገባልም ብሏል።

ከምንም በላይ ሃይማኖት በሚያስተምረው መንገድ ሰዎችን በማክበር፣ እርስ በእርስ በመተዛዘንና በመዋደድ በተለይም የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት እንዲሁም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በየመጠለያው የሚገኙ ወገኖችን በማሰብ መሆን እንዳለበት አመልክቷል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል (ገና) የሰላም፣ የጤና እና የብልጽግና እንዲሆን መልካም ምኞቱን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም