ብርጋዴል ጀኔራል አሊጋዝ ገብሬን ጨምሮ በአራት ከፍተኛ የመከላከያ መኮንኖች ላይ የመጨረሻ የምርመራ ጊዜ ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 28 ቀን 2013 (ኢዜአ) ብርጋዴል ጀኔራል አሊጋዝ ገብሬን ጨምሮ በአራት ከፍተኛ የመከላከያ መኮንኖች ላይ የመጨረሻ የምርመራ ጊዜ ተሰጠ።

የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት በእነ ብርጋዴር ጄኔራል አሊጋዝ መዝገብ አራት ተጠርጣሪ ጦር መኮንኖችና ሌሎች ከሕወሃት ጋር ሲሰሩ ነበር በተባሉ የመከላከያ መኮንኖች መዝገብ ተመልክቷል።

ችሎቱ በቅድሚያ የተመለከተው በአንድ መዝገብ የቀረቡት የመከላከያ ስልጠና ኮሌጅ አመራር በነበሩት ብርጋዴል ጀኔራል አሊጋዝ ገብሬና ኮሎኔል አብርሃ ታደለ ገብሩ፣ እንዲሁም ኮሎኔል ገብረስላሴ በላይና ሻለቃ ወልዳይ ሳምረን ጉዳይ ነው።

ተጠርጣሪዎቹ በመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ጥቃት እንዲፈጸም በማድረግ፣ ለትግራይ ልዩ ሃይል መረጃ በማቀበልና በትግራይ ክልል ወታደራዊና የሬዲዮ መገናኛ ስልጠና በመስጠት መጠርጠራቸውን መርማሪ ፖሊስ ገልጿል።

መኮንኖቹ ከትግራይ እስከ አዲስ አበባ በሰራዊቱ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም በተሰራው ህቡዕ አደረጃጀት የስራ ክፍፍል እንደነበራቸውም ፖሊስ አስረድቷል።

ለአብነትም የመከላከያ ሰራዊት የሬዲዮ መገናኛዎችን ወደ ትግራይ ክልል ስለመላካቸው ጠቅሷል።

ፖሊስ በተጠርጣሪዎች ላይ ቀሪ የምርመራ ስራዎችን ለማከናወን ተጨማሪ የ14 ቀናት ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ደንበኞቻችን ፈጸሙት ስለተባለው ወንጀል በዝርዝር አልቀረበም፤ ፖሊስ ከዚህ በፊት ሰራሁት ካለው የተለዬ መረጃ ይዞ ባለመምጣቱ ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል።

ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ካደመጠ በኋላ መርማሪ ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀናት ለመጨረሻ ጊዜ 9 ቀናት በመፍቀድ ለጥር 7 ቀን 2013 ዓ.ም የፖሊስ ምርመራ መዝገብን ለመስማት ቀጠሮ ይዟል።

ፍርድ ቤቱ በተጨማሪም የመከላከያ ሰራዊትን ምስጢር ለህወሃት ቡድን አቀብለዋል፤ በስልክም ወታደራዊ አመራር ሰጥተዋል በሚል የተጠረጠሩ በምስራቅ ዕዝ 13ኛ ክፍለ ጦር አመራር የነበረው ሌተናል ኮሎኔል ምሩጽ ወልደአረጋይ ጉዳይን ተመልክቷል።

የፖሊስን የምርመራ መዝገብ በመመልከትና የቃል ክርክር በማድመጥ በተጠርጣሪው ላይ የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ የሬዲዮ ኦፕሬተር ባለሙያ በነበሩት በመቶ አለቃ ማረ ታደለና ሌላ ባልደረባቸው ችሎት ቀርበዋል።

ተጠርጣሪዎቹ የተሰጣቸውን ሃላፊነት ተገን በማድረግ ህወሃት መሸነፍ የለበትም በሚል የጦር መሳሪያዎችን ወደ ትግራይ ክልል በመላክ ወንጀል ስለመጠርጠራቸው ተመልክቷል።

መርማሪ ፖሊስ ለተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጥያቄውን ተከትሎ ችሎቱ 12 ቀናትን ፈቅዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም