በእሳት አደጋ ንብረት ለወደመባቸው የምግብና አልባሳት ድጋፍ ተደረገ

60

ሆሳዕና፤ታህሳስ 28/2013(ኢዜአ) የሀድያ ዞን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፅህፈት ቤት በሚሻና ሌሞ ወረዳ በእሳት አደጋ ንብረት ለወደመባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች 466 ሺህ ብር ግምት ያለው ምግብና አልባሳት ድጋፍ አደረገ።

ጽህፈት ቤቱ 124 ኩንታል የምግብ እህል፣ 42 ሊትር ዘይትን ጨምሮ ፍራሽና ሌሎች አልባሳቶችን ትላንት ጉዳት ለደረሰባቸው በድጋፍ አበርክቷል።

የጽህፈት ቤቱ  ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ በወቅቱ እንደገለጹት ድጋፍ የተደረገው በወረዳዎቹ በደረሰ የእሳት አደጋ የንብረት ውድመት ለደረሰባቸውና ለተፈናቀሉ ወገኖች ነው።

ፅህፈት ቤቱ በሚቻለው ሁሉ ተጎጂዎችን ለማቋቋም እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

በሚሻ ወረዳ ጌሜዶ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አበበ ሎንሰቆ እንዳሉት በእሳት አደጋው ንብረታቸው ሙሉ በሙሉ መውደሙን ተናግረዋል::

በአሁን ወቅት በድንኳን ተጠልለው እንደሚገኙና በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በአደጋው ንብረታቸው ሙሉ በሙሉ እንደወደመ  የገለጹት በሌሞ ወረዳ የኦሞሸራ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ከበደ ቲሮሮ ስለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቲዮስ ሎምበሶ "ምክንያቱ ባልታወቀ መንገድ በተከሰተ ቃጠሎ ጉዳት የደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በዘላቂነት ለማቋቋም ይሰራል" ብለዋል።

የተጎጅዎችን የዕለት ደራሽ የምግብና አልባሳት ችግራቸውን ለመቅረፍና በዓሉን ታሳቢ በማድረግ ድጋፉ መደረጉን አስታውቀዋል።

በሀድያ ዞን ሶስት ወረዳዎች በቅርቡ ምክንያቱ ባልታወቀ የእሳት አደጋ 25 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ንብረት መውደሙንና 482 ቤተሰቦች መፈናቀላቸውን የዞኑ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም