ምክትል ከንቲባዋ ለአቅመ ደካሞች፣ ለፌደራልና ለአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት የገና በዓል ስጦታዎችን አበረከቱ

63

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለአቅመ ደካሞች እንዲሁም ለፌዴራልና ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖች አባላት የገና በዓል ስጦታ አበረከቱ። 

ምክትል ከንቲባዋ በጉለሌ ክፍለ ከተማ አስተባባሪነት የተዘጋጁትን ስጦታዎች ነው ያበረከቱት።

በዚህም 73 የታደሱ የአቅመ ደካማ ነዋሪዎች ቤቶችን ቁልፍ ያስረከቡ ሲሆን ለበዓል ማክበሪያ የሚውሉ 40 በሬዎች፣ 114 በጎችና 200 ዶሮዎችን ለአቅመ ደካሞችና ለፀጥታ አባላቱ አስረክበዋል።

ምክትል ከንቲባ አዳነች በመዲናዋ እየተከናወኑ ያሉ የአቅመ ደካሞችን ቤቶች ማደስና ሌሎች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባራት የአብሮነት ማሳያዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የጉለሌ ክፍለከተማ ዋና ሥራ አስፈጸሚ አቶ አባወይ ዮሐንስ በበኩላቸው በድንበር ተሻጋሪ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችና በክፍለከተማው ወጣቶች በርካታ የበጎ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

የአቅመ ደካሞችን ቤት ከማደስ ባሻገር ለበዓል ማክበሪያ የሚሆኑ ቁሳቁስና የበዓል መዋያ መሰጠቱን ገልፀዋል።

በተመሳሳይ ምክትል ከንቲባዋ በጉለሌ ክፍለከተማ ድንበር ተሻጋሪ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች በሱሉልታ ወረዳ የተገነባውን ባለ 3 ክፍል ቤት ከቤት እቃዎች ጋር ለአንድ አካል ጉዳተኛ ወጣት አስረክበዋል።

ለቤቱ ግንባታና የቤት እቃዎች ማሟያ ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ መደረጉ ተገልጿል።

በርክክቡ ወቅት የሱሉልታ ከተማ ከንቲባ አቶ ሰለሞን አበበ እንደገለፁት "ጉርብትና በመደጋገፍ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ከአዲስ አበባ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች የመጣው ተነሳሽነት የሚያስመሰግን ነው" ብለዋል።

ይህን በጎ ተግባር አጠናክሮ በማስቀጠል በሌሎች ዘርፎችም መድገም እንደሚገባ ተናግረዋል።

የጉለሌ ክፍለከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አባወይ ዮሐንስም ጉለሌ እና ሱሉልታ አጎራባች በመሆናቸው በጋራ መልማት አለባቸው ነው ያሉት።

የጉለሌ ክፍለ ከተማ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች "ስራችን በክፍለ ከተማ ብቻ መታጠር የለበትም" በሚል አጎራባቹን ሱሉልታ ወረዳን አካተው በርካታ የበጎ ፍቃድ ሥራዎች እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል።

"ይሄ በጎ ተግባር በዚህ ብቻ አያበቃም" ያሉት አቶ አባወይ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ሌሎች ሥራዎችን በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የመኖሪያ ቤቱን የተረከበው ወጣት ፍቅሩ ናዳድ በበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች በተደረገለት እገዛ መደሰቱን ገልጾ ለወጣቶቹ ምስጋና ቸሯል።

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይህ አብሮነት በሁሉም ዘርፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

አብሮነቱን በሁሉም ዘርፍ በማጠናከርና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን በማዳበር በጋራ መልማትና ማደግ እንደሚቻል ያወሱት ምክትል ከንቲባዋ ለዚህም የከተማ አስተዳደሩን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም