የጸረ-ተባይ ኬሚካል አጠቃቀም ጉድለት የማር ምርታቸውን እንዳሳነሰባቸው የአምባሰል ወረዳ አናቢዎች ገለጹ

ደሴ፣ታህሳስ 27/2013( ኢዜአ ) በደቡብ ወሎ ዞን ከባለሙያ ምክረ ሃሳብ ውጭ በገፍ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው የፀረ ተባይና ፀረ አረም ኬሚካል የማር ምርት ከግማሽ በታች እንዲቀንስ ማድረጉን የአምባሰል ወረዳ ንብ አናቢ አርሶ አደሮች ገለፁ።

በአምባሰል ወረዳ የ02 ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ጀማል መሃመድ ለኢዜአ እንደገለጸው ቀደም ሲል ከአንድ ቀፎ እስከ 40 ኪሎ ግራም የማር ምርት ያገኝ እንደነበረ አስታውሷል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከአንድ በንብ መንጋ ከተሞላ ቀፎ ከቀደመው ሩብ ያክሉን ብቻ እያገኘ መሆኑን ጠቅሶ አርሶ አደሩ ፀረ አረምና ፀረ ተባይ ኬሚካል ባልተገባ መልኩ ጥቅም ላይ በመዋሉ የንብ መንጋው ለአደጋ መጋለጡን ገልጿል።

በፊት ከነበረው 40 ቀፎ ወደ 20 ዝቅ ማለቱንም ጠቁሞ፤መልሶ ተጠቃሚ ለመሆንም የአርሶ አደሩን የኬሚካል አጠቃቀም በባለሙያ ታግዞ እንዲሰጥ ማድረግ እንደሚገባ ተናግሯል።

ሌላው የ03 ቀበሌ ነዋሪ አቶ መኮነን ዳምጠው በበኩላቸው ንብ ማነብ ከአያት ቅድመ አያቶቻችው የወረሱት ሙያ እንደሆነና ከልጅነታቸው ጀምሮ ንብ እያነቡ በሚያኙት ገቢ ቤተሰባቸውን እንደሚያስተዳድሩ ተናግረዋል።

በዓመት ሁለት ጊዜ ከአንድ ቀፎ እስከ 40 ኪሎ ግራም ድረስ ስለሚያገኙ ተጠቃሚ እንደነበሩም አስታውሰዋል።

አሁን ግን በየጊዜው ያለ ገደብ ከግብርና ባለሙያዎች ምክር ውጭ በሚረጭ ጸረ ተባይ ኬሚካል ንቦች ማር ማምረት ከማቆማቸውም ባለፈ እየሞቱባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአርሶ አደሩ የኬሚካል አጠቃቀም በተገቢው መንገድ እንዲከናወን የግብርና ባለሙያዎችና የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የአምባሰል ወረዳ እንሰሳት ሀብት ልማት ተጠሪ ጽህፈት ቤት ንብ ርባታና ሐር ልማት ባለሙያ አቶ አያሌው መኮነን በበኩላቸው አምባሰል ወረዳ በማር ምርት ታዋቂ በመሆኑ ምርቱም ተፈላጊ ነበር።

ይሁን እንጂ በፌደራል ደረጃ የወጣው የኬሚካል አጠቃቀም አዋጅ ተግባራዊ ባለመሆኑ በዘፈቀደ በሚረጭ ኬሚካል የማር ምርቱ በየአመቱ እያሽቆለቆለ መምጣቱ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

“ከሦስት ዓመታት በፊት በወረዳው ከ10 ሺህ በላይ የነበረው ቀፎ ወደ 6 ሺህ 850 ዝቅ ማለቱን ጠቁመው፤የማር ምርቱም በእጥፍ ቀንሷል” ብለዋል፡፡

በወረዳው ከ30 እስከ 50 ኪሎ ግራም ምርት ከአንድ ቀፎ ይገኝ እንደነበረ አስታውሰው፤አሁን ላይ ከ5 እስከ 10 ኪሎ ግራም ዝቅ ማለቱን ገልጸዋል፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን እንሰሳት ሀብት ልማት ተጠሪ ጽህፈት ቤት የንብና ሐር ልማት ባለሙያ አቶ ጥላሁን አበራ እንደገለጹት በዞኑ በፊት ከነበረው ከ200 ሺህ በላይ ቀፎ ከ300 ቶን በላይ የማር ምርት ይገኝ ነበር፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጸረ ኬሚካል ርጭት እየቀነሰ 138 ሺህ ቀፎ መድረሱን ጠቁመው ከ200 ቶን በታች የማር ምርት እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ችግሩን በጊዜያዊነት ለማቃለል 237 አባላት ያሉት ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ንቦች በማይወጡበት ጊዜ ጸረ ተባይ ኬሚካል እንዲረጭና በሰው ኃይል መታረም የሚችል አረም በሰው እንዲታረም እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዞን ከ30 ሺህ በላይ ንብ አናቢዎች ያሉ ሲሆን በዚህ ዓመት እስከ አሁን በተካሄደ እንቅስቃሴ አንድ ሺህ 85 ቶን የማር ምርት መገኘቱን ከተጠሪ ጽህፈት ቤቱ ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም