ተቋርጦ የሰነበተው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በተስተካካይ ጨዋታዎች ሰኞ ይጀምራል - ኢዜአ አማርኛ
ተቋርጦ የሰነበተው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በተስተካካይ ጨዋታዎች ሰኞ ይጀምራል
አዲስ አበባ ግንቦት 4/2010 ላለፉት ሁለት ሳምንታት ተቋርጦ የቆየው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የፊታችን ሰኞ በሚካሄዱ ተስተካካይ ጨዋታዎች እንደሚጀምር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ። የኢትዮጵያ ዳኞች እና ታዛቢዎች ማህበር 'ዳኞች ለሶስት ሳምንታት ማንኛውንም ውድድር እንደማይዳኙ በመግለጽ የአቋም መግለጫ ማውጣቱን' ተከትሎ የሊጉ ጨዋታዎች ተቋርጠው ቆይተዋል። ፌዴሬሽኑ ከማህበሩ ጋር ግንቦት 2 ቀን 2010 ዓ ም ባደረገው ውይይት ፕሪሚየር ሊጉ እንዲቀጥል ስምምነት ላይ በመደረሱ ሰኞ በሚደረጉ ተስተካካይ ጨዋታዎች ይጀመራል። በዚሁ መሰረት ሰኞ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ አስር ሰአት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮ ኤሌትሪክ ይጫወታሉ። በደጋፊዎች ረብሻ ተቋርጦ የነበረውና እስከ መጀመሪያው አጋማሽ የተካሄደው የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲና መቐለ ከተማ ቀጣይ 45 ደቂቃ ሽሬ እንዳስላሴ ላይ ከቀኑ በዘጠኝ ሰአት ይካሄዳል። በአዳማ አበበ በቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማ ከወላይታ ድቻ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ የሚጫወቱ ይሆናል። ግንቦት 10 ቀን ክልል ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከወላይታ ድቻ፣ መቐለ ከተማ በሜዳው ቅዱስ ጊዮርጊስን በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይገጥማል። የፕሪምየር ሊጉ መደበኛ መርሃ ግብሮች ረቡዕ ግንቦት 15 ቀን በሚካሄዱ የ23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እንደሚጀምሩም ፌዴሬሽኑ አስታወቋል። በዚህም መሠረት ረቡዕ ግንቦት 15 ቀን በአዲስ አበባ ስታድየም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከቀኑ ስምንት ሰአት፣ ደደቢት ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ከቀኑ አስር ሰአት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ድሬዳዋ ከተማ በሜዳው ከመከላከያን ሲገጥም፣ በሃዋሳ ስታዲየም ሃዋሳ ከተማ ከፋሲል ከተማ፣ በአዳማ አበበ በቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማ ከመቐለ ከተማ፣ በሶዶ ስታዲየም ወላይታ ድቻ ከሲዳማ ቡና በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይጫወታሉ። በሰበታ ስታዲየም ወልዲያ ከኢትዮጵያ ቡና እና በጅማ ስታዲየም ጅማ አባጅፋር ከአርባምንጭ ከተማ በተመሳሳይ ዘጠኝ ሰአት ላይ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል። ጅማ አባጅፋር ፕሪምየር ሊጉን በ39 ነጥብ ሲመራ፣ መቐለ ከተማ በ35 ነጥብ እንዲሁም ደደቢት እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በ33 ነጥብ ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ይዘዋል።