ከማህበረሰብ ዓቀፍ የጤና መድህን አባላት 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ዓመታዊ መዋጮ ተሰበሰበ

74

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ጤና መድህን ኤጀንሲ ከማህበረሰብ ዓቀፍ የጤና መድህን አባላት 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ዓመታዊ መዋጮ መሰብሰቡን አስታወቀ።

በዚህ ዓመት የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተጠቃሚ ዜጎችን ቁጥር ወደ 40 ሚሊዮን ከፍ ለማድረግ እንደሚሰራም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ጤና መድህን ኤጀንሲ የ2013 ዓ.ም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የአባልነት እድሳትና ምዝገባ ዘመቻን አስመልክቶ ዛሬ በተሰጠ መግለጫ ላይ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬህይወት አበበ እንደተናገሩት፤ የጤና መድህን ተጠቃሚዎች ቁጥር 32 ሚሊዮን ደርሷል።

መጪውን የጥር ወር "የጤና መድህን ወር" ብሎ በመሰየም የአባልነት እድሳትና አዳዲስ አባላትን የመመዝገብ ተግባር እንደሚከናወንም ተናግረዋል።

በየደረጃው የሚገኙ የጤና መድህን አስፈጻሚ አካላት የአባልነት ምዝገባ ዘመቻውን የመምራትና የማስተባበር ስራ እንደሚያከናውኑም ገልጸዋል።

መገናኛ ብዙሃንና ታዋቂ ግለሰቦችን በመጠቀም ስለ ዘመቻው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እንደሚከናውኑም ነው የጠቆሙት።

ከጤና መድህን አባላት 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ዓመታዊ መዋጮ መሰብሰቡን ገልጸው፤ ከዚህም ውስጥ አባላቱና ቤተሰቦቻቸው ላገኙት የሕክምና አገልግሎት ከ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ለጤና ተቋማት ክፍያ መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የማህበረሰብ ዓቀፍ የጤና መድህን በ2003 ዓ.ም በ13 ወረዳዎች በሙከራ ደረጃ የተጀመረና አሁን በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ተስፋፍቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም