በዘንድሮው የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች በዓል የህዝቦችን ትስስርና አንድነትን የሚያጎሉ ስራዎች ተከናውነዋል--አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
በዘንድሮው የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች በዓል የህዝቦችን ትስስርና አንድነትን የሚያጎሉ ስራዎች ተከናውነዋል--አቶ አደም ፋራህ

አዳማ ታህሳስ 27/2013 (ኢዜአ) በዘንድሮው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በዓል ህዝቦችን ትስስር የሚያጠናክሩና አንድነትን የሚያጎሉ ስራዎች መከናወናቸውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ- ጉባኤ አደም ፋራህ ገለጹ።
በዓሉ የነበረው ገፅታና ክንውኖችን አስመልክቶ በአዳማ ከተማ እየተገመገመ ነው።
በግምገማው መድረክ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ- ጉባኤ አደም ፋራህ እንደተናገሩት ህገ መንግሥቱን ዜጎች እንዲገነዘቡትና እንዲጠብቁት የበዓሉን አጋጣሚ በመጠቀም ሰፊ ስራዎች ተከናውነዋል።
በተለይ ህብረብሔራዊ አንድነትን ከማፅናትና ሀገራዊ አንድነት እንዲጠናከር ዘርፈ ብዙ ተግባራት እንደተከናወኑም ገልጸዋል።
ህዝቦች እርስ በራሳቸው እንዲተዋወቁ ፣ባህላቸውንና ማንነታቸውን እንዲያሳውቁ የተከናወኑት ስራዎች ከወትሮው በዓላት በተለየ እንደነበር አፈጉባኤው አውስተዋል።
ይህም በተለይ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ትስስር የሚያጠናክሩና አንድነትን ያጎሉ እንደነበሩ ገልጸዋል።
በምክር ቤቱ የዘንድሮው በዓል አስተባባሪ አቶ ሙስጠፋ ናስር በበኩላቸው በዓሉ ህገ መንግስቱ ለህዝቦች ያጎናፀፈውን መብት በአግባቡ የሚተገበርበት ሂደቶች በስፋት የተቃኙበት እንደነበር ተናግረዋል።
በዚህም ህገ መንግስታዊና ፌዴራላዊ ስርዓት አጠባበቅ ላይ ከ1 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ግንዛቤ አግኝተዋል ብለዋል።
በዓሉ የጎረቤት ሀገራት ህዝቦች ጭምር የተሳተፉበትና ብዙሃነት ለሀገር አንድነት ውበት መሆኑን የተገነዘቡበት እንደሆነም ጠቅሰዋል።
በበዓሉ በነበረው ሂደት ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በትክክል ባህላዊ እሴቶቻቸውንና ማንነታቸውን ያሳዩበት ነው ብለዋል።
ለበዓሉ ስኬት ሁሉም ክልሎች ያሳዩት ቁርጠኝነትና የአንድነት መንፈስ ከምን ጊዜውም በላይ ትኩረት ያገኘ መሆኑንም አስተባባሪው አስረድተዋል።
መገናኛ ብዙሃንም የበዓሉን አጠቃላይ ገፅታ ወደ ህዝቡ በማድረስ ትልቅ ሚና የተጫወቱበትና ሰፊ ሽፋን የሰጠበት እንደነበረም አቶ ሙስጠፋ ተናግረዋል።
በግምገማው መድረክ የበዓሉ ኮሚቴ የነበሩ አካላትና የሚዲያ ተቋማት አመራሮች እየተሳተፉ ነው።
15ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል"እኩልነትና ሕብረብሔራዊ አንድነት ለጋራ ብልፅግና" በሚል መሪ ሀሳብ መከበሩ ተመልክቷል።