የወሳኝ ኩነት ምዝገባን ለማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተደረገ

ታህሳስ 26/2013 (ኢዜአ) የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ በአገሪቱ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ለማጠናከር ከኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማትና ከኢትዮጵያ ሚድ ዋይፎች ማህበር ጋር የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈራረመ።

በኢትዮጵያ ያለው የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ከሌሎች አገሮች አንጻር ''እጅግ ዝቅተኛ'' እንደሆነ ይገለጻል።

የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጂብ ጀማል እንደገለጹት ስምምነቱ የአገሪቱን  የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አፈጻጸም ለማሻሻል የሚረዳ ነው።

ለዚህም በምዝገባው ሚና ካላቸው ጋር በትብብርና በቅንጅት መስራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

የሃይማኖት ተቋማት ለተከታዮቻቸው የጋብቻ፣ የፍቺ፣ የልደትና የቀብር አገልግሎት የሚሰጡ እንደመሆናቸው የወሳኝ ኩነት ምዝገባን የሚያሻሽል ለውጥ ለማምጣት ጉልህ ድርሻ እንዳላቸውም ገልጸዋል።

የሃይማኖት ተቋማቱ ተወካዮች በበኩላቸው፤ የወሳኝ ኩነት ምዝገባን ማካሄድ ለማህበረሰቡም ለመንግስትም ጠቀሜታ እንዳለውም ተናግረዋል።

በዚህም ህዝቡን ማስተማርና በማሳወቅ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ምዝገባው የሚፈለገውን ያህል ውጤት እንዲያመጣም ከኤጀንሲው ጋር ተባብረውና ተቀናጅተው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ አባል

የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዘነበ አካለ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ በአገሪቱ ለማሻሻል የተደረሰው ስምምነት ለውጥ እንደሚያመጣ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በተለይም በመረጃ ላይ የተመሰረተ ትክክለኛና ተአማኒ ምዝገባ ለመፍጠር ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም