በአገልግሎትና አምራች ዘርፍ የተሰማራ ሰው በሥራው ለመሻሻል የካይዘን አሰራር መተግበር እንዳለበት ተመለከተ

49

ቢሾፍቱ ታህሳስ 26/2013( ኢዜአ) በአገልግሎትና አምራች ዘርፍ የተሰማራ ሰው ሁሉ በሥራው መሻሻልን ለማስቀጠል የሚጠቅመውን የካይዘን አሰራር መተግበር እንዳለበት የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት አመለከተ።

ኢንስቲትዩቱ የካይዘን ትግበራ የልምድ ልውውጥ አውደ ጥናት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቢሾፍቱ ከተማ እያካሄደ ነው።

በአውደ ጥናቱ መልዕክት ያስተላለፉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ያኢ እንዳሉት ከውጭ ይገቡ የነበሩ  የለውጥ ፍልስፍ እና አሰራሮች  የሚፈልጉትን አመራር ባለማግኘታቸው አሁን ላይ ተቀዛቅዘዋል።

የለውጥ ፍልስፍ እና አሰራሮች የተፈጠሩባቸው ሀገራት በነበረው የስልጣኔ ደረጃና የተማረ የሰው ሃይል ምጣኔ በሚበቃ ልክ ኢትዮጵያ  ባለመድረሷም ለመተግበር አስቸጋሪ ሆኖ መቆየቱን አስረድተዋል።

ሆኖም ጃፓን በቴክኖሎጂ ምርታማነትና ጥራት የዓለም ቁንጮ የሆነችው  ካይዘን ሁሉም ሰው በተሰማራበት ስራ  በመተግባር የማይቋረጥ መሻሻል ውስጥ ሊቀጥል በመቻሉ ነው ብለዋል።

ካይዘን ከቤት አያያዝ እና ትምህርት ቤትን ጨምሮ በአምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ቀለል ካሉ አሰራሮች አንስቶ እስከ ከባድ ፍልስፍናን በመተግበር  መሻሻልን ለማስቀጠል እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ሳይንሱን ተግብረው በአፍሪካ ደረጃ ለምርታማነትና ጥራት ሽልማት የበቁ ተቋማት እንደ አብነት ተወስደው ሌሎቹም ሊተገብሩት እንደሚገባ አመልክተዋል።

በአውደ ጥናቱ በካይዘን ትግበራ ውጤት በማስመዝገብ ልምዳቸውን ለሌሎች ካጋሩት ተቋማት መካከል ጥቁር አባይ ትራንስፖርት  ኩባንያ፣ የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ደቡብ ክላስተርና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ይገኙበታል።

በጥቁር አባይ ትራንስፖርት ኩባንያ  የካይዘን ተጠሪ የሆኑት አቶ እድገት ጎበዜ ኩባንያቸው ፍልስፍናውን ስራ ላይ ማዋል ከጀመረ ከ2009ዓ.ም አንስቶ የሰራተኞቹን እርካታ 95 በመቶ በላይ አድርሷል፤ የሰዓት ብክነትንም በትልቁ ቀንሷል ብለዋል።

በኮምቦልቻ አገልግሎት መስጫ ቦታቸው ውስጥ  በፈጠራ ስራ ጋራዥ መገንባታቸው እንደ ትልቅ ስኬታቸው አውሰተዋል።

የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የደቡብ ክላስተር ስራ አስኪያጀ አቶ ዘመነ ለገሰ በበኩላቸው ካይዘን በመተግበራቸው በተለይም በመድሃኒት ብክነት የአለም አቀፉን የጤና ድርጅት መስፈርት ማሟላታቸውን ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ አምራች እና ቅሬታ አልባ አገልግሎት ሰጪ ተቋም መገንባት የካይዘን ፍልስፍና መሆኑ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም