መገናኛ ብዙሃን ህዝቡን በማንቃት የፀረ ሙስና ትግሉ ባለቤት እንዲሆን ማገዝ አለባቸው-- ኮሚሽኑ

41

አዳማ ታህሳስ 26/2013 (ኢዜአ) የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ህዝቡ በማንቃት የፀረ ሙስና ትግሉ ባለቤት እንዲሆን ለማስቻል ማገዝ እንዳለባቸው የፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወዶ አጦ ተናገሩ።

ኮሚሽኑ" ስነ ምግባርን በመገንባትና ሙስናን በመከላከል ረገድ የሚዲያ ተቋማት ሚና"  መሪ ሀሳብ  ለመገናኛ ብዙሃን ተቋማት አመራሮች ያዘጋጀው መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

ምክትል ኮሚሽነር ወዶ አጦ  እንደገለጹት የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ህዝቡን በማንቃትና የፀረ ሙስና ትግሉ ባለቤት እንዲሆን ለማስቻል ማገዝ ይጠበቅባቸዋል።

በተለይ ህዝቡ የሙስና ትግሉን የዕለት ተዕለት አጀንዳው እንዲያደርግ ከመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ጋር በቅንጅት ለመስራት የሚያስችል የጋራ ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ መድረኩን እንዳዘጋጁ  ተናግረዋል።

ምክትል ኮሚሽነሩ የመንግስት አመራሮችን ከአሰራር አንፃር በሚፈጥሩት ክፍተትና ከህብረሰተሰቡ በሚያጎድሉት አገልግሎት ተጠያቂ እንዲሆኑ ከማስቻል አኳያ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ሰርተዋል የሚል እምነት የለኝም ብለዋል።

ከለውጡ ወዲህ የታየው የመገናኛ ብዙሃን  መነቃቃት የፀረ ሙስና ትግሉ ሀገራዊ አጀንዳና ተቋማዊ እንዲሆን የተቀረፁ ስትራቴጅዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የዘርፉ አመራሮችና በየደረጃው ያሉ ሙያተኞች ህዝቡን ማንቃትና የትግሉ ባለቤት እንዲሆን ማስቻል አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል።

በተለይ በትውልድ ቀረፃና የስነ ምግብር ግንባታ፣ በየተቋማቱ የተደራጁ የስነ ምግባር መከታተያ መኮንኖች ከአመራሮች ጋር ያለምንም ጫና ተቀናጅተው እንዲሰሩ የተሰጣቸውን ተልዕኮ ከዳር እንዲደርስ የሚደረገው ጥረት ማገዝ እንደሚገባም  አመልክተዋል።

በኮሚሽኑ የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክተርና በመድረኩ ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ ተስፋዬ ሻኒቢ በበኩላቸው መድረኩ የተሰናደው ጠንካራ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችለው የሚዲያ ተቋም በፀረ ሙስና ትግል በንቃት ለማሳተፍ ነው ብለዋል።

በተለይ በቀጣይ አስር ዓመት መሪ እቅድ ውስጥ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በትብብር ለመስራት እንደሆነም አስረድተዋል።

በመንግስታዊ ተቋማትና የልማት ድርጅቶች ውስጥ የፀረ ሙስና ትግሉ ተቋማዊ ይዘት እንዲኖረው የስነ ምግባር መከታተያ መኮንኖች ማደራጀትና ወደ ትግሉ ማስገባት ብቻ በቂ አይደለም ብለዋል።

በክልልና ፌዴራል የመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉትን ከፅዳት ሰራተኛ እስከ አመራር ድረስ ሁሉም ሀብቱን እንዲያስመዘግብ ማድረግና በትምህርት ቤቶች ላይ የፀረ ሙስና ክበባት በማደራጀት ተማሪዎችን ከወዲህ በስነ ምግባር ለማነፅ ጭምር እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በሀገሪቱ ባሉ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ስራዎች ይሰራሉ፤  ሚዲያዎች ይህን ንቅናቄ በመምራት ጭምር የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያን በፀረ ሙስና ትግል ከአፍሪካ ቀዳሚ ለማድረግና ህዝቡ መብቱን በገንዘብ እንዳይገዛ በማድረግ በኩል የመገናኛ ብዙሃን  ሚና የላቀ መሆኑን  አመልክተዋል።

የመገናኛ ብዙሃን  ዘርፍ  በተመለከተ በመድረኩ ጽሑፍ ያቀረቡት የኢትዮጰያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ  ሚዲያው የሀገሪቱ  አራተኛ የዴሞክራሲ ምሰሶ መሆን አለበት ብለዋል።

መገናኛ ብዙሃን የየተቋማቱን ብልሹ አሰራር በማጋለጥ ረገድ መስራት ይኖርባቸዋል  ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በተለይ የምርመራ ጋዜጠኝነት በማጠናከር ላይ በትኩረት መሰራት እንደሚገባ  አመልክተዋል።

ሙስና ለኢትዮጵያ ብልፅግና እንቅፋት እንዳይሆን መገናኛ ብዙሃን ህዝቡን በማንቃትና የአጀንዳው ባለቤት ማድረግ፣ አሁን በሀገሪቱ  ያለው ውስብስብ የሙስና ችግሮች እንዲወገዱ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል።

በመድረኩ  የመንግስትና  ግል   መገናኛ ብዙሃን   አመራሮች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም