የተሰጠን ሽልማት ይበልጥ ለመስራትና ውጤታማ ለመሆን አነሳስቶናል-- ተሸላሚ አርሶ አደሮች

67

አዲስ አበባ ታህሳስ 26/2013 (ኢዜአ) የተሰጠን ሽልማት ይበልጥ ለመስራትና ውጤታማ ለመሆን አነሳስቶናል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ተሸላሚ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በግብርና ሴክተር ስኬት ላስመዘገቡ አርሶና አርብቶ አደሮች በአዳማ ከተማ የዕውቅና መርሐግብር ተካሂዷል።

በዚህም ከ600 በላይ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች፣ ከ80 በላይ የምርምር ተቋማት፣ የግብርና ሴክተሩን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የፈጠራ ውጤቶችን ያፈለቁ ግለሰቦችና ሙያተኞች እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ተሸላሚዎች "የተሰጠን ሽልማት ይበልጥ ለመስራትና ውጤታማ ለመሆን አነሳስቶናል" ብለዋል።

በመንግስት የማዳበሪያና ምርጥ ዘር አቅርቦት የተሟላ በመሆኑና የባለሙያ እገዛ ተደርጎላቸው  በመስራታቸው ውጤታማ መሆናቸውንና ለሽልማት መብቃታቸውንም አንስተዋል።

ከጅማ ዞን የመጡት አርሶ አደር ብዙየሁ መኮንን እና ከምዕራብ ወለጋ የመጡት አርሶ አደር ከበደ በሬሳ  ለሽልማት የበቁት በቡና ልማት ተሰማርተው ለምርት ጥራት ትኩረት አድርገው በመስራታቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ሽልማቱ በበለጠ ትጋት ለመስራት የሞራል ስንቅ እንደሆናቸው  የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎች፣መንግስት ውጤታማነታቸውን ለማሳደግ የብድር አገልግሎት እንዲያመቻችላቸውና ስራቸውን አስፍተው የሚሰሩበት ሁኔታ እንዲፈጥር ጠይቀዋል።

የግብርና ምርት ላኪዎች፣ ዩኒየኖች፣ በግብርና ስኬት ያስመዘገቡ ሴቶችና ወጣቶች እንዲሁም መገናኛ ብዙሃን እውቅናው ከተሰጣቸው መካከል ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም