ለአዕምሯዊ ንብረት መብቶች መከበር መገናኛ ብዙሃን የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ለአዕምሯዊ ንብረት መብቶች መከበር መገናኛ ብዙሃን የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 25/2013( ኢዜአ) ለአዕምሯዊ ንብረት መብቶች መከበር መገናኛ ብዙሃን ለማህበረሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር የድርሻቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ጠየቀ።
የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት በንግድ ምልክት፣ በፓተንት፣ በቅጅና ተዛማጅ መብቶች ምንነት ላይ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰጥቷል።
የጽህፈት ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳሉ ሞሲሳ፤ በተመዘገቡ የአእምሯዊ ፈጠራ መብቶች ላይ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የመብት ጥሰት እየተፈፀመ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም የፈጠራ ባለቤቶች ህዝብን ሲያገለግሉ ቆይተው ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም ሳያገኙ ለችግር እየተዳረጉ እንዳሉ ገልጸዋል።
የሰዎችን የአዕምሮ ንብረት ያለፈቃድ መጠቀም ወንጀል መሆኑንና ተጠያቂነትን እንደሚያመጣ ህብረተሰቡ አውቆ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ በማስገንዘብ መገናኛ ብዙሃን የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል።
የአእምሯዊ ንብረት እውቀትና ግንዛቤን በማህበረሰቡ ውስጥ በማስረጽ በኩልም እንዲሁ።
ጽህፈት ቤቱ በዋናነት ለሰው ልጅ የአእምሮ ፈጠራ ውጤቶች የጥበቃ ስራን እንሚያከናውን የገለጹት አቶ እንዳሉ፣ የፈጠራው ባለቤቶች መብቶቻቸውን አስከብረው ተጠቃሚ የሚሆኑበት ስርአት መዘርጋቱንም ጠቁመዋል።
"ሀገር፣ ማህበረሰቡና ባለሙያዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለመብቶቻቸው ተመጣጣኝ የሆነ ክፍያ በስራዎቻቸው ተሰብስቦ ለባለመብቶች የሮያሊቲ ክፍያ እንዲከፈል ጥረት እየተደረገ ይገኛልም" ብለዋል።
ተቋማት ለሚገዟቸው የፈጠራ ምርቶች የሚያደርጓቸውን ውሎች አስመልክቶም ጽህፈት ቤቱ የሙያና የምክር አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት የኮፒራይት የሥራ ሂደት ኃላፊ አቶ ናስር ኑሩ በበኩላቸው በአንዳንድ የሬድዮና የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ያለባለቤቶቹ ፈቃድ ሥራዎቻቸው ጥቅም ላይ ሲውሉ እየታየ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ችግን ለመከላከል ባለመብቶች በማህበር ተደራጅተው ጥቅማቸውን እንዲያስከብሩ ለማድረግ ሥራዎች መጀመራቸውን ጠቁመዋል።
በህብረተሰቡና በባለሙያው በኩል ያለውን ክፍተት ለመሙላትም መሰል የግንዛቤ ማስጨበጫዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
አእምሯዊ ንብረት ማለት በሰው ልጅ አእምሮ የሚፈጠሩ የፈጠራ ሥራዎችን የሚመለከት ሲሆን እነዚህ የፈጠራ ሥራዎች እንደማንኛውም ቁሳዊ ሀብት በንብረትነት የሚታወቁበትን አግባብ የያዘ ሥርዓት ነው፡፡
የአእምሯዊ ንብረት ጥቅም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዕውቅና ያገኘው የኢንደስትሪያዊ ንብረት ጥበቃን የሚመለከተውና እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1883 የተፈረመውን ዓለም አቀፉን የፓሪስ ስምምነትና በ1886 የተፈረመውን የሥነ ጽሑፍና ስነ ጥበብ ሥራዎች ጥበቃን የተመለከተው የበርሊን ስምምነትን ተከትሎ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።