የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ ልማት የ15 ዓመታት መሪ እቅድ ተዘጋጀ

ሀዋሳ፤ታህሳስ 24/2013 (ኢዜአ) የፌዴራል ተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን በቀጣዮቹ 15 ዓመታት በሀገሪቱ በሚገኙ ስምጥ ሸለቆዎች የሚከናወኑ የተፋሰስ ልማት መሪ ዕቅድ ማዘጋጀቱን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ የዕቅዱን የትኩረት አቅጣጫ ማስተዋወቅን ዓላማ ያደረገ የምክክር መድረክ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በባቱ ከተማ ተወያይቷል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዳነች ያሬድ በወቅቱ እንዳሉት መሪ ዕቅዱ ተግባራዊ የሚደረገው በኦሮሚያ፣ደቡብና ሲዳማ ክልሎች በሚገኙ ዝዋይ፣ሻላ፣ሀዋሳ፣ አባያና  ጫሞ ሐይቆች አካባቢ ነው።

በመሪ እቅዱ መሠረት ከሚከናወኑ ስራዎች መካከል የሐይቆቹ መገኛ ስፍራዎችን ከብክለት መጠበቅ፣ የውሃ ጥራትና መጠናቸውን በየጊዜው በመለካት መፍትሄ መስጠት ይገኝበታል ብለዋል።

የጎርፍና የድርቅ ክስተት ጉዳት መቀነስና ቅንጅታዊ አሠራርን ማጎልበት የዕቅዱ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውንም ዋና ዳይሬክተሯ አስረድተዋል።

የውሃ ሃብቶቹን በአግባቡ ከመጠቀምና የተቀናጀ ህጋዊ መሠረት ከማስያዝ ባለፈ ተፋሰሶቹን ከብክለትና ከጥፋት ለመታደግ ያስችላል ብለዋል።

በባለስልጣኑ የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደበበ ደፈርሳ በበኩላቸው፤ መሪ እቅዱ የውሃ መስኖ አጠቃቀም ከማሳደግና ከውሃ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ድንገተኛ አደጋዎች ለማስቀረት ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል።

በልማት ስራዎቱ በተፋሰሱ ዙሪያ የሚገኙ 13 ሚሊዮን የህብረተሰብ ክፍሎች በዘላቂነት ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ መያዙንም ገልጸው፤ ለዕቅዱ አተገባበር ከ10 ቢሊዮን 500 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት እንደሚያስፈልግ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አስታውቀዋል።

ውሃ ለሁለንተናዊ ልማትና ብልፅግና ወሳኝና ውስን የተፈጥሮ ሀብት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብርሃም አዱኛ ናቸው።

እንደሳቸው ገለፃ በሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ ችግሮች ሳቢያ የተፋሰሶች መጠንና ጥራታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል።

ለዚህ መንስዔ የሆነው በአጠቃቀም ጉድለት ብክለትና ብክነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የደኖችና ዕጽዋቶች መመናመን እንዲሁም የውሃ ሃብት አስተዳደር፣ ለማገገሚያ የተሰጠው አሳታፊና ቅንጅታዊ አሠራር ትኩረት ማነስን ጠቅሰዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ችግሩን ለማቃለል በወሰደው ጠንካራ እርምጃ ለውጦች እንደመጡ ገልፀው፤ በተለይ የኢንዱስትሪና ዩኒቨርሲቲ ትስስር፣ የወሳኝ አካላት ተሳትፎና በባለቤትነት መንፈስ መፍትሄ ለማምጣት  የተደረገው ርብርብ ለለውጡ መገኘት አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል።

በቀጣይም በውሃ ሃብት ላይ እየተከሰቱ ያሉ እንቦጭና መሰል ችግሮችን መከላከል፣ ተፋሰሶችን ማልማትና ደለሎችን ማስወገድ፣ የተፋሰስ ዳርቻዎችን ዘላቂ ጥቅም በሚሰጥ መልኩ ማልማት  የዕቅዱ አካል ተደርጎ  መቀጠል አለበት ብለዋል።

የስምጥ ሸለቆ ሓይቆች ተፋሰስ ልማት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ የውሃ ሴክተሮችን  አሳታፊ፣ ቅንጅታዊ አሠራር፣ የዓላማና የግብ አንድነት በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለውም አስረድተዋል።

ለዕቅዱ ስኬታማነት በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ያልተቆጠ  ጥረት እንዲያደርጉ ዶክተር አብርሃም አሳስበዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የደቡብ ክልል የአከባቢ፣ ደንና የአየርን ብረት ለውጥ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ግዛቴ ጉጄ በሰጡት አስተያየት መሪ ዕቅዱን ለማሳካት ህዝቡን የመፍትሄው አካል በማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ከታህሳስ 23/2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው መድረክ  በዕቅዱ አተገባበርና የውሃ ዳርቻ አካላትን ለመጠበቅና ለመከለል በተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ  ውይይት ተደርጎበታል።

በመድረኩ  ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ከኦሮሚያ፣ ደቡብና  ሲዳማ ክልሎች የተወጣጡ ባለድርሻ አካላትና የዘርፉ ምሁራን ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም