ሀገራዊ ሪፎርም እና ምርጫ 2013

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 25/2013 ( ኢዜአ) ሀገራዊ ሪፎርም እና ምርጫ 2013 በመንግስቱ ዘውዴ /ኢዜአ/

የዴሞክራሲ ሥርዓት ህዝብ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ወይም በሁለቱም መንገድ የስልጣን ባለቤትነቱን የሚያረጋግጥበት ስርዓት ነው። ይህም የዜጎች እኩልነት የሚረጋገጥበት ህዝብ የሚያስተዳድረውን አካል ያለምንም ተፅዕኖ ከመካከሉ መርጦ ሥልጣን የሚሰጥበት ነው። ዴሞክራሲ በሕዝብ ይሁንታ ላይ የተመሰረተ የመንግስት አስተዳደር ሥርዓት የመፍጠር፣ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የማረጋገጥ ጉዳይ ነው፡፡ የህዝብ ይሁንታና የስልጣን ባለቤትነት ከሚረጋገጥባቸው መንገዶች አንዱ ምርጫ ነው።

በአንድ ሀገር ውስጥ ምርጫ የሚደረግበት ዋነኛ ምክንያት መራጮች መሪዎቻቸውን ለመምረጥና ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ፣ የፖለቲካ መረጋጋትና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ የዜጎችን የመወሰን መብት ለማጎናጸፍ፣ ማናቸውም ፍላጎቶች በህጋዊ መንገድ ብቻ ለመምራት በአጠቃላይ ዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን የሚለማመዱበትን ሁኔታ ለመፍጠር መሆኑን በዚህ ዙሪያ የተጻፉ ሰነዶች ያመለክታሉ። የፖላንድ ዩኒቨርሲቲ ምሁር ፕሮፌሰር Waldemar Wojtasik “functions of elections in democratic system” በሚል ርእስ ባቀረቡት የጥናት ጽሑፍ ላይ የምርጫ ጠቀሜታዎችን በሰባት ከፍለውታል። እነዚህም አመኔታ ለጣሉበት አካል የስልጣን ውክልና ለመስጠት፣ ካሉት አማራጮች ብቁ ነው ብለው የገመቱትን የፖለቲካ መሪ ለመምረጥ፣ የስልጣን ህጋዊነት ለማረጋገጥ፣ ስልጣንን ለመቆጣጠር፣ ተጠያቂነትን ለማስፈን፣ የፖለቲካ ፕሮግራሞችን ለመንደፍ እና የህዝብ አስተያየቶችን ለማስተካከል የሚሉት ናቸው።

ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ (1948) አንቀጽ 21 “ሁሉም ሰው በሀገሩ መንግስት አስተዳደር ውስጥ በቀጥታ ወይም ነፃ በሆነ ሂደት በተመረጡ ተወካዮች አማካኝነት ተሳትፎ የማድረግ መብት አለው…የመንግስት ስልጣን በህዝብ ፍላጎትና ስምምነት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት፤ ይህም በህዝብ ፍላጎትና ስምምነት ዓለም አቀፍና ለሁሉም እኩል በሆነና በሚስጢር በሚደረግ የድምጽ መስጠት ምርጫ ወይም ተመጣጣኝ በሆነ ድምጽን የመግለጽ ሁኔታ በየጊዜውና በትክክል በሚፈጸሙ ምርጫዎች የሚረጋገጥ መሆን አለበት።” ሲል ይደነግጋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የተከናወነ ነው ለማለት የሚያስችሉ መስፈርቶች በግልጽ የተቀመጡ ሲሆን ከሂደቱ ጀምሮ ቢያንስ የሚከተሉትን መሰረተ ሃሳቦች መያዝ ይኖርበታል።

  • የምርጫ መርሆዎች- ይህምማለት እኩል፣ ፍትሐዊና ነጻ የውድድር ዕድል ለሁሉም ተፎካካሪዎች መስጠትን፣ እያንዳንዱ መራጭ አንድ ድምጽ ያለው መሆኑ፤ የሁሉንም ዜጎች የመምረጥ መብት ማረጋገጥን፣ እጩዎች በምርጫ ሂደት እኩል መብት ያላቸው መሆኑን፣ እንዲሁም እያንዳንዱ መራጭ በምርጫ ውጤት ላይ እኩል ተጽዕኖ እንዳለው ማመንን ያጠቃልላል፤
  • የሕዝባዊነት መርህ- ይህም ህዝቡ በምርጫ ሂደት ላይ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚችል፣ በምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ገለልተኛ ታዛቢዎች እንዲኖሩ ማድረግን የያዘ ነው፤
  • የምርጫ ነፃነት መርህ- መገናኛ ብዙሀን በነፃነት እንዲዘግቡ ማድረግን፣ የምርጫ ነፃነት በሕግና በሞራል ማዕቀፍ የተደገፈ ማድረግን፣ ማንኛውም ዜጋ ያለማንም ጫና በፈቃደኝነት በምርጫ መሳተፍን ያጠቃልላል፤
  • የምርጫ ሁለንተናዊነት- ፆታ፣ ዜግነት፣ መደብ ወይም ሌላ ዝምድና፣ የገቢ እና የትምህርት ደረጃ፣ የርዕዮተ ዓለም እምነት ሳይለይ ለምርጫ በህግ የተፈቀደ ዕድሜ ላይ የደረሰ ማንኛውም የአገሪቱ ዜጋ የሚሳተፍበት መሆን፣ ከማንኛውም ጫናዎች ነፃ መሆንን እንዲሁም የምርጫ ሚስጥራዊነትን የያዘ ነው።   

በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ የተጀመረው በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነው ፓርላማ ከ1924 እስከ 1928 ዓ.ም የቆየው ሲሆን በ1923 ዓ.ም ተዘጋጅቶ ሥራ ላይ በዋለው የመጀመሪያው የተጻፈ ህገ መንግሥት መሠረት የተቋቋመ ነው። በወቅቱ የም/ቤት አባላትን የሚመርጡት ንጉሠ ነገሥቱ ነበሩ። ከ1948 ዓ.ም ጀምሮ ህዝቡ ራሱ እንደራሴዎቹን በቀጥታ እንዲመርጥ መፈቀዱን ተከትሎ ከ1948 እስከ 1967 ዓ.ም በየአራት ዓመቱ አምስት ተከታታይ ምርጫዎች ተካሂደዋል።

የደርግ ወታደራዊ መንግሥት ከ1967-1983 ዓ.ም ሀገሪቱን ያስተዳደረ ሲሆን በ1967 ዓ.ም በጥቅምት ወር ከልዩ ልዩ ወታደራዊ ክፍሎችና መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ 6ዐ ሰዎችን ያቀፈ የመማክርት ጉባኤ የመሠረተ ሲሆን ጉባኤው እስከ 1968 ዓ.ም ድረስ ሲሰራ ቆይቶ የተበተነ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ደርግ ከአስር ዓመት በኋላ በ1979 ዓ.ም 835 አባላት ያሉት የሥራ ዘመናቸውም አምስት ዓመት የሆኑ ባለ አንድ ሸንጎ ምክር ቤት በምርጫ እንዲሰየሙ ያደረገ ቢሆንም ዕጩውን የሚጠቁመውም፣ የሚያስመርጠው ኢሠፓ (የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ) ነበር፡፡ በወታደራዊ የደርግ ዘመነ መንግሥት ሥርዓቱ ሶሻሊስታዊ ርዕዮት ከመሆኑም ባሻገር የመድብለ ፓርቲ ስርዓትም ስላልነበረ ምርጫዎች ተካሄዱ ለማለት አይቻልም።

በ1987 ዓ.ም የጸደቀው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በሀገራችን የመድበለ ፓርቲ ስርዓት እንዲኖርና  በየአምስት ዓመቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ምርጫ እንዲካሄድ ደንግጓል። በዚህ ድንጋጌ መሠረት እስካሁን አምስት ተከታታይ ምርጫዎች ማለትም በ1987፣ በ1992፣ በ1997፣ በ2002 እና በ2007 ዓ.ም የተካሄዱ ሲሆን ስድስተኛው ምርጫ በያዝነው 2013 ዓ.ም ግንቦት ወር ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።

በኢፌዴሪ መንግስት ከተካሄዱ አምስት ምርጫዎች የተሻለና ለየት ያለ ትኩረት ያገኘው በ1997 ዓ.ም የተካሄደው ምርጫ ሲሆን በአንፃራዊነት የቅድመ ምርጫ ሂደቱ ዴሞክራሲያዊ እንደነበር በወቅቱ የተሳተፉ የዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ሪፖርት ያመለክታል። የወቅቱ የቅንጅት ፓርቲ አመራር አቶ ግርማ ሠይፉ በ2009 ዓ.ም “የተከበሩት…በሕወሓት/ኢህአዴግ ፖለቲካ ፓርላማ” በሚል ርእስ በፃፉት መጽሐፍ የቅድመ ምርጫ ምዕራፍ የመገናኛ ብዙሃን፣ የሲቪል ማህበራት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ የጎላ እንዲሆን ተደርጎ እንደነበርና ግልጽ ውይይትና ክርክር በማድረግ ምርጫው እንዲካሄድ ስለመደረጉ አስፍረዋል።

ይሁን እንጂ በድህረ ምርጫ ሂደቱ አሸናፊውና ተሸናፊው ውጤቱን በጸጋ ከመቀበልይልቅ ወደ ውዝግብ ገብተው ነበር። የምርጫ ውጤት ይፋ ከተደረገ በኋላ ምርጫ ቦርድን ሳይጠብቁ ገዥው የኢህአዴግ ፓርቲ እና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በየበኩላቸው “አሸንፈናል” የሚል መልእክት ለህዝቡ  አስተጋቡ። በሁለቱም በኩል “ምርጫው ተጭበርብሯል” የሚሉ አቤቱታዎች ቀርበዋል። በተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎችም ምርጫው ስለመጭበርበሩ በመረጋገጡ በድጋሚ እንዲካሄድ ተደርጓል።    በታዛቢነት ከቀረቡት ተቋማት መካከል የአውሮፓ ህብረት የታዛቢዎች ቡድን ምርጫው ዓለም ዓቀፍ መስፈርቶች የተጓደሉበት፣ እኩል የመወዳደሪያ ሜዳ ያልነበረውና ለገዢው ፓርቲ ባደላ መልኩ የተካሄደ እንደሆነ ገልጿል።

ምርጫ 97 የድምጽ ቆጠራው ይፋ መሆንን ተከትሎ በገዥው ፓርቲና በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ከፍተኛ ውጥረት በመፈጠሩ ብዙ ንጹሃን ህይወታቸው ያጡበትና በርካቶች ለእስር፣ ለእንግልትና ለስደት የተዳረጉበት ክስተት ያስተናገደ ከመሆኑም በላይ ለዴሞክራሲ ተከፍቶ የነበረው ምዕራፍ መልሶ የተዘጋበት ሆኖ አልፏል። ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ከዚያን ጊዜ በኋላ የጸረ ሽብርተኝነት ህጉን ጨምሮ የተለያዩ አፋኝ ህጎችን በማውጣት የግል መገናኛ ብዙሃን፣ ሲቪል ማህበራት፣ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጨዋታው ጠቅልለው እንዲወጡ ብቻ ሳይሆን ኢህአዴግ አውራ ፓርቲ ሆኖ ሊወጣ የሚችልበትን ስልት ቀይሶ በተግባር ያዋለበት እንደነበር የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ይናገራሉ። ከዚህ በተጨማሪ የምርጫ ቦርድ ገለልተኛነት ላይ ጠንከር ያለ ጥያቄ ሲቀርብበት ቆይቷል።

በተፎካካሪ ፓርቲዎችም በኩል በግልጽ በተነደፈ የፖሊሲ አማራጭ ላይ ተመስርቶ ለውድድር ከመቅረብ ይልቅ በተበታተነና ባልተደራጀ መልኩ ወደ ስልጣን ለመምጣት መፈለግ፤ የምርጫ ህጎችን አክብሮ በመንቀሳቀስ በኩል ጉድለቶች መኖር፤ የድምጽ መስጫ ጊዜው ሲቃረብ አቋርጦ መውጣት፤ አሊያም የምርጫ ውጤት መገለጽን ተከትሎ የተለያዩ ምክንያቶችን መደርደር፤ ያገኙትን የህዝብ ድምጽ አክብሮ ከመቀበል ይልቅ ማንገራገር በዚህም ያልተፈለገ ግጭት፣ አለመረጋጋት እና ቀውስ መከሰት የተለመዱ ሂደቶች ነበሩ። የዴሞክራሲ ምህዳሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበበ በመምጣቱ ምክንያት በየአካባቢው በተቀሰቀሰ ህዝባዊ አመጽ በተለያዩ መስኮች ሀገራዊ ለውጥ እንዲመጣ አስገድዷል። ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በውጭ ሀገራት በተለያዩ መንገዶች ትግል ሲያካሂዱ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ አንቂዎች/አክቲቪስቶች/ እና ታዋቂ ሰዎች እንዲሁም ከውጭ ሆነው ዘገባ ሲያሰራጩ የነበሩ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ ተደርጓል።   

ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ ከመጣ በኋላ መንግስት በከፍተኛ ትኩረት ሪፎርም ካደረገባቸው ተቋማት መካከል አንዱ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ነው። ከዚህ ጎን ለጎን የምርጫ አዋጆችና ደንቦች እንዲሁም የፖለቲካ ምህዳሩ ላይ ተጽእኖ የነበራቸው የጸረ ሽብርተኝነት፣ የበጎ አድራጎትና የሲቪክ ማህበራት፣ የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጆችን ጨምሮ ሌሎች ህጎችና ደንቦች ላይ ማሻሻያ ተደርጎባቸዋል። ብዙውን ጊዜ ገለልተኛነቱ ላይ ትችት ሲቀርብበት የነበረው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም በአዲስ መልኩ እንዲደራጅ ተደርጓል። የቦርዱ አመራሮችም ገለልተኝነቱን ማረጋገጥ የሚያስችሉ የምርጫ አዋጅን ጨምሮ የተለያዩ መመሪያዎችንና የአሰራር ማኑዋሎችን በማዘጋጀት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ከሲቪክ ማህበራት፣ ከመገናኛ ብዙሃንና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን አድርገዋል።

የተሻሻለው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1133/2011 የተሻሻለበትን ዓላማ ሲያብራራ “የዜጎችን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ከማንኛውም አካል ነፃ በሆነ የምርጫ አስፈፃሚ ተቋም እንዲመራ፤ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባላትን አመላመልና አሿሿም ግልጽ ለማድረግ እና በተወዳዳሪ ድርጅቶችና በመራጮች ዘንድ ያለውን ተአማኒነትና የማስፈጸም አቅም ለማሳደግ እንዲረዳ ነው፡፡” ሲል ይገልጻል። በተመሳሳይ ምርጫን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባን እና ተያያዥ ሥነ ምግባርን የሚገዛው ህግ “የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011” ተብሎ ተሻሽሎ ተዘጋጅቷል። ዓላማውም ምርጫ ሁሉን አቀፍ፣ ነፃ፣ ፍትሃዊና ሠላማዊ እንዲሆን ለማድረግ፣ የዓለም አቀፍ የምርጫ መርሆዎችን አካቶ እንዲይዝ ለማስቻል፣ ዜጎች በቀጥታና በነፃነት በመረጧቸው ተወካዮች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ስልጣናቸውን በተግባር ላይ ለማዋል፣ ፓለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራምና ዓላማቸውን ማራመድ እንዲችሉ፣ ዜጎችና ፓርቲዎች በምርጫ ሥርዓት ውስጥ የሚኖራቸውን መብትና ግዴታ ለመደንገግ እና በምርጫ ሂደት ለሚነሱ አለመግባባቶች አስተዳደራዊና የዳኝነት መፍትሄ የሚሰጡ ተቋማትን እና አሰራራቸውን ለመወሰን ነው፡፡

ኢትዮጵያ ዘንድሮ የምታካሂደው ሀገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ በበርካታ ምክንያቶች ታሪካዊና በጉጉት የሚጠበቅ ነው። የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ “ምርጫ 2013 ቁልፍ የሽግግር ምዕራፍ” በሚል ርዕስ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና ከሲቪክ ማህበራት ተወካዮች ጋር ውይይት በተካሄደበት ወቅት ባቀረቡት ጽሁፍ የዘንድሮው ምርጫ ቀደም ሲል ከተደረጉ ምርጫዎችም ይሁን ከዚህ በኋላ ከሚካሄዱ ምርጫዎች የተለየ፣ ታሪካዊና ጉልህ ፋይዳ ያለው መሆኑን አብራርተዋል። ምርጫው ወሳኝ ከሚያደርጉት ምክንያቶች መካከል ከሀገራዊ ለውጥ በኋላ የሚካሄድ የመጀመሪያው ምርጫ መሆኑና ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለሚደረገው ሽግግር ትልቅ መገለጫ መሆኑን ነው። ሁለተኛው ጉዳይ ከዚህ በፊት ከተካሄዱ ምርጫዎች በተለየ መልኩ ነፃነት ባለበት ሁኔታ የተሻለ ፉክክር ይካሄድበታል ተብሎ በህብረተሰቡ ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ ምርጫ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የሚመረጡ የክልልም ሆነ የፌዴራል የህዝብ ወኪሎች ቀጣዩን የሀገሪቱን የፖለቲካና የኢኮኖሚ አቅጣጫ የሚወስኑበት ስለሆነ የዘንድሮውን ምርጫ ታሪካዊነትና ፋይዳ ጉልህ ያደርገዋል ሲሉ ዶ/ር ጌዲዮን አብራርተዋል።

ዘንድሮ የሚካሄደው ምርጫ በዚህ ደረጃ ወሳኝና ታሪካዊ ከሆነ ምርጫው ነፃ፣ ፍትሀዊና ተአማኒ ሊሆን ይገባዋል። ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ በምርጫው ሂደት ድርሻ ያላቸው ተዋንያን የየበኩላቸው ኃላፊነት በአግባቡ ሲወጡ ነው። ባለፉት ምርጫዎች የተስተዋሉ ድክመቶች እንዳይደገሙ ዜጎች፣ መንግሥት፣ የሲቪክ ማህበረሰቡና የመገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው። ህግ የማክበርና የማስከበር፣ የምርጫውን ሂደት ነፃ፣ ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የማድረግ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው አማራጭ ሃሳባቸውን እንዲያቀርቡ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ከመንግስት የሚጠበቅ ሃላፊነት ነው።

የፖለቲካ ፓርቲዎችም አማራጭ ፖሊሲዎቻቸውን በተገቢው መልኩ በመቅረጽ የስነምግባር መርሆዎችን አክብረው መንቀሳቀስ፣ አባላቶቻቸውንና ደጋፊዎቻቸው ህግ አክብረው እንዲንቀሳቀሱ የማድረግ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በገለልተኝነት ዜጎችን ማንቃት፣ የምርጫ ሂደቱ ሠላማዊ ፉክክር ያለበት እንዲሆን የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው። ከዚህ ባሻገር የመገናኛ ብዙሃን ያለምንም ወገንተኝነት ለዜጎች ወቅታዊ፣ ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃ ማድረስ ይጠበቅባቸዋል።  ዜጎችም በምርጫው ሂደት በንቃት በመሳተፍ የመምረጥና የመመረጥ መብታቸውን መጠቀም፣ ምርጫው ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም