አምቦ ዩኒቨርሲቲ ለአንድ ተመራማሪና መምህር የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጠ

9

አምቦ፣ ታህሳስ 25/2013 (ኢዜአ) አምቦ ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአንድ ተመራማሪና መምህር የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማእረግ ሰጠ፡፡

ዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ የሰጠው ለዶክተር እንድሪያስ ዘውዴ ነው።

ፕሮፌሰር ኢንድሪያስ ዘውዴ በዩኒቨርሲቲው ለ31 ዓመታት በመምህርነት ሙያ ያገለገሉና በእንሰሳት ህክምና ዙሪያ 60 ምርምሮችን በማካሄድ ለህትመት ያበቁ ናቸው።

ፕሮፌሰሩ ጥናትና ምርምሮቻቸውን በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ያሳተሙና በማኅበረሰብ አገልግሎት በርካታ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ናቸው።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ታደሰ ቀነአ ፕሮፌሰር ኢንድሪያስ ዩኒቨርሲቲው ኮሌጅ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ ሁኔታዎች ባልተሟሉበት ጊዜ ሳይሰለቻቸው ለዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ እገዛ ካደረጉ ምስጉን መምህራኖች አንዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ጊዜ ከ27 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ ዩኒቨርሲቲው ትምህርትን በጥራት ለመስጠት ምሁራንን የማብቃት ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ፕሮፌሰር ኢንድሪያስ ዘውዴ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ለሰጣቸው የፕሮፌሰርነት ማእረግ አመስግነው "ማእረጉ የበለጠ ተግቼ እንድሰራ አነሳስቶኛል" ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በሚቀጥሉት 10 አመታት ለ40 ተመራማሪዎች የፕሮፌሰርነት ማእረግ ለመስጠት እቅዶ እየሰራ መሆኑ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም