ማኅበረሰቡ በመተከል ዞን በንጹሃን ዜጎች ላይ በተፈፀመው ድርጊት የተሳተፉትን በማጋለጥ ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል

49

ታህሳስ 24/2013 (ኢዜአ) ማኅበረሰቡ በቤኒሻንጉል ጉምዝ መተከል ዞን በንጹሃን ላይ ለደረሱ ጥቃቶች ተጠያቂ የሆኑ አካላትን ለሕግ እንዲቀርቡ በማድረግ ሃላፊነነቱን እንዲወጣ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሃይማኖት አባቶች የመተከል ዞን የተለያዩ ማኀበረሰብ አባላት በዘር፣ በሃይማኖትና በቀለም ሳይለያዩ ይኖሩበት የነበረ አካባቢ መሆኑን ገልጸዋል።

በዞኑ የሚኖሩ ዜጎች ተካፍለው በመብላት በመረዳዳትና በመተጋገዝ የሚኖሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ የአብሮነት እሴት መሸርሸሩንና አብሮ በኖረው ማኅበረሰብ መካከልም የተደራጀ የጥፋት ሃይል ገብቶ የሕይወት ማጥፋት፣ ማፈናቀልና ዘረፋ እንዲስፋፋ አድርጓል ብለዋል።

የተደራጀው ቡድን በመተከል ዞን በሚኖረው ማኅበረሰብ ላይ የሚሰነዘር ጥቃት እንጂ የሕዝብ ለሕዝብ ግጭት አለመሆኑን፤ ሕዝቡ አሁንም በሠላም አብሮ መኖር እንደሚፈልግ ተናግረዋል።

በንጹሃን ዜጎች ላይ በተፈጸሙ ኢ-ሠብዓዊ ድርጊቶች ላይ የተሳተፉ አካላት ለሕግ እንዲቀርቡ ሁሉም ዜጋ በመተከል ዞን ከተቋቋመው የፌዴራል የጸጥታ ግብረሃይል ጋር መስራት እንዳለበት ነው የገለጹት።

በመተከል ዞን የተቋቋመው የፌዴራል የጸጥታ ግብረሃይል መሪ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ በበኩላቸው ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት የጸጥታ ሃይሉ፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።

ሕዝቡን የማረጋጋት ስራ በቀዳሚነት ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ ያለ ተግባር መሆኑም ገልፀዋል።

በመተከል ዞን ጸጥታን ከማስከበር ባለፈ ሕዝቡ ያሉበትን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎችም ችግሮች  መፍታት የሚያስችል ተግባር ጎን ለጎን እንደሚከናወንም ገልጸዋል።

የሕወሓት ቡድን ከዚህ አካባቢ እየመለመለና እያሰለጠነ በአካባቢው ሠላም እንዲያደፈርሱ ይጠቀምባቸው እንደነበረ መታወቁን ጠቁመዋል።

ሕግ ባለበት አገር የንጹሃን ሕይወት መጥፋት፣መፈናቀልና ንብረት መውደም እንደሌለበትና የጸጥታ ችግሩም በአጭር ጊዜ እንደሚፈታም ሌተናል ጄኔራል አስራት ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የተቋቋመው የፌዴራል የጸጥታ ግብረ ሃይል የመተከል ዞንን የጸጥታ ማስከበር ስራ መረከቡ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም