ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዳርት ሻምፒዮና ዛሬ ተጀመረ

አዲስ አበባ ግንቦት 4/2010 ከስድስት ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ 96 ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉበት 14ኛው የኢትዮጵያ ዳርት ሻምፒዮና ዛሬ በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ተጀምሯል። ውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች በታዳጊና አዋቂ ነጠላ ጥንድ እና ድብልቅ (ሴትና ወንድ) በሚሉ 13 ዘርፎች ተከፋፍሎ ይካሄዳል። ዳርት አነስተኛ ቀስቶችን ለኢላማ በተዘጋጀ ቦርድ በመወርወር ነጥብ የሚቆጠርበት የስፖርት አይነት ነው። የኢትዮጵያ ዳርት ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን አላምረው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ውድድሩ መካሄዱ ስፖርቱ ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ያደርጋል። በአህጉር አቀፍና በዓለም አቀፍ መድረኮች ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳደሩ ብቁ ተወዳዳሪዎች ለማፍራትና ለመመልመል ውድድሩ ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥር ገልጸዋል። ውድድሩ ክልሎች የእርስ በእርስ ግንኙነት እንዲፈጥሩና የባህል ልውውጥ እንዲያደርጉ የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል። በውድድሩ ላይ የአማራ፣ጋምቤላና ኢትዮ ሶማሌ ክልሎች በበጀት እጥረትና ተወዳዳሪዎች ባለማዘጋጀታቸው አለመሳተፋቸውን ጠቅሰዋል። የዳርት ስፖርት በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች በስፋት እየተዘወተረ ሲሆን በአህጉር አቀፍና በዓለም አቀፍ መድረኮች መሳተፍ የፌዴሬሽኑ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነም ነው አቶ ጥላሁን ያስረዱት። በውድድሩ ላይ በእያንዳንዱ ዘርፍ አሸናፊ የሚሆኑ ተወዳዳሪዎች የሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማት እንደሚያገኙ ጠቁመዋል። በተጨማሪም ጥቅምት 3 እና 4 ቀን 2011 ዓ.ም በግብጽ ርዕሰ መዲና ካይሮ በሚካሄደው የአፍሪካ የዳርት ሻምፒዮና ለመሳተፍ ስፖንሰር የማፈላለግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አክለዋል። የዳርት ጨዋታ ከስፖርቱ ባሻገር፤ ለተመስጦ፣ በራስ ለመተማመን፣ ለዓይንና ለእጅ እንቅስቃሴ እንዲሁም የአእምሮ ንቃትን ለመጨመር ጠቃሚ እንደሆነ የስፖርቱ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በኢትዮጵያ ስፖርቱ በ1980 ዎቹ መዘውተር መጀመሩን መረጃዎች ያመለክታሉ። የበጀትና የመጫወቻ ቁሳቁስ እጥረት እንዲሁም የመወዳደሪያ ቦታ አለመኖር የዳርት ስፖርት በኢትዮጵያ በሚፈለገው ደረጃ እንዳያድግ እንዳደረገው ይነገራል። የኢትዮጵያ ዳርት ፌዴሬሽን በ1990 ዓ.ም ነው የተቋቋመው። የዳርት ስፖርት በመካከለኛው ክፍለ ዘመን በእንግሊዛውያን ዘንድ ይዘወተር እንደነበር ታሪክ ያስረዳል። በወቅቱ የወይን መጥመቂያ በርሜል የታችኛውን ክፍል ኢላማ በማድረግ በቀስት ይጫወቱም ነበር።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም