ነዋሪነታቸውን በአሜሪካ ያደረጉት ዶክተር አስረሱ ምስክር ለእምቦጭ አረም ማስወገድ ዘመቻ የ800 ሺህ ብር ቁሳቁሶች ለገሱ

106

ጎንደር፣ ታህሳስ 24 ቀን 2013 (ኢዜአ) አሜሪካ የሚኖሩ በጎ አድራጊ ዶክተር አስረሱ ምስክር እምቦጭን ለማስወገድ እየተሳተፉ ላሉ አርሶአደሮች የሚውል ግምታቸው 800 ሺህ ብር የሆነ አልባሳትና የጽዳት ቁሳቁሶችን ለገሱ፡፡

የጣና ሀይቅና ሌሎች የውሃ አካላት ኤጀንሲ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም ልየው እንደገለጹት፤ የጎንደር አካባቢ ተወላጅ የሆኑት ዶክተር አስረሱ ካስረከቡዋቸው ቁሳቁሶች መካከል የእምቦጭ አረም ለማስወገድ የሚውል 300 አልባሳት ይገኝበታል፡፡

በተጨማሪም 500 የእጅ ጓንቶችና ከ2ሺህ በላይ የግል ንጽህና መጠበቂያ ሳሙናዎች እንዳሉበት ገልጸዋል።

አልባሳቱና የእጅ ጓንቶቹ ከጣና ሃይቅ ላይ አረሙን በእጃቸው የሚያስወግዱ አርሶአደሮች በእባብና ሌሎች ጎጂ ነፍሳት እንዳይጎዱ ለመከላከያነት የሚያገለግሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ዶክተር አስረሱ ምስክር ተወካይ አቶ ሚሊኪያስ ታዬ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የጣና ሐይቅ አዋሳኝ በሆነው ሸሃ ጎመንጌ ቀበሌ በመገኘት ድጋፉን በኤጀንሲው በኩል በአረም ማስወገድ ዘመቻው ለተሳተፉ አርሶ አደሮች አስረክበዋል፡፡

ተወካዩ በወቅት እንደተናገሩት፤ በአሜሪካን የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ሐይቁ አካባቢ ለሚኖሩ የአርሶአደሩ ልጆች ትምህርት ቤት ለመገንባት እቅድ አላቸው፡፡

ሀይቁን የወረረውን አረም በማስወገድ በጉልበታቸው መሳተፍ ከጀመሩ ስምንት ዓመታት ማስቆጠራቸውን የተናገሩት ደግሞ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የሸሃ ጎመንጌ ቀበሌ አርሶአደር ካሳው ታግሎ ናቸው፡፡

"ሀይቁ ውስጥ ገብተን አረሙን በምናስወግድበት ወቅት በጊንጥ፣ እባብና ሌሎችም ነፍሳት ጉዳት ሲደርስብን ቆይቷል" ያሉት አርሶአደሩ የተሰጣቸው ቁሳቁስ ችግሩን ለማቃለል እንደሚረዳቸው እንደሚያቃልልላቸው ተናግረዋል፡፡

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ትዛሉ ተገኘ በበኩላቸው ድጋፍ የተደረገላቸው አልባሳት ውሃ የማያስገባ በመሆኑ በእጅና እግራቸው ላይ ሲደርስባቸው የነበረውን የማሳካክ ችግር ለመፍታት እንደሚረዳቸው ገልጸዋል።

ለሁለት ወራት በዘለቀው ሀገር አቀፍ የእምቦጭ አረም ማስወገድ ዘመቻ በሀይቁ ላይ በየቀኑ ከ12ሺ በላይ ሰዎች ሲሳተፉ ቆይተዋል፡፡

ለዘመቻው ስኬታማነትም የፌደራልና ክልል መንግስታዊ ተቋማት እስካሁን ድረስ 30 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ከጣና ሀይቅና ሌሎች የውሃ አካላት ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም