በደብረ ማርቆስ የንባብ ባህልን ለማዳበር የሚያግዝ የመጻህፍት አውደ ርዕይ ተከፈተ - ኢዜአ አማርኛ
በደብረ ማርቆስ የንባብ ባህልን ለማዳበር የሚያግዝ የመጻህፍት አውደ ርዕይ ተከፈተ
ደብረ ማርቆስ፣ ታህሳስ 23/2013 (ኢዜአ) በደብረ ማርቆስ ከተማ የንባብ ባህልን ለማዳበር የሚያግዝ የንባብ ሳምንትና የመጻህፍት አውደ ርዕይ ዛሬ ተከፈተ።
''መጽሐፍት የእውቀት ገበታ መዛግብት የዘመን ትውስታ ናቸው'' በሚል መሪ ቃል የተከፈተው የንባብ ሳምንትና አውደ ርዕይ ለአራት ቀን የሚቆይ ነው።
አውደ ርዕዩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ ከደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሀዲስ አለማየሁ የባህል ተቋም ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።
የኤጀንሲው ዳታ ቤዝ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ግዛው ዋቅጅራ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ አውደ ርእዩ የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና የአካባቢው ማህበረሰብ የማንበብ ልምድ እንዲያዳብሩ ማገዝን ዓላማ ያደረገ ነው።
"ኤጀንሲው በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ከተሞች በመቀሳቀስ የንባብ ሳምንት፣ የመዛግብት ቀንንና የመጻህፍት አውደ ርእይን በማዘጋጀት ኀብረተሰቡ የማንበብ ባህልን እንዲያዳብር እያደረገ ይገኛል" ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ የመጻህፍት ሽያጭና የንባብ መድረኮች እንደሚዘጋጁም አስታውቀዋል።
ለህዝብ ቤተ መጻህፍትና ትምህርት ቤቶች ከአንድ ሺህ በላይ አጋዥና የማገናዘቢያ መጻፍህት እንደሚለገስም ጠቁመዋል።
ኤጀንሲው ባለፉት ስድስት ዓመታት ከባለድርሻ አካላት ጋር መድረኮችን በማዘጋጀቱ የህብረተሰቡ መጽሐፍትን ገዝቶ የማንበብ ባህል እየተሻሻለ መምጣቱን ማረጋገጥ እንደተቻለ አቶ ግዛው ተናግረዋል።
ኤጀንሲው በጋራ መኖሪያ ቤቶች ተንቀሳቃሽ ቤተ መጻህፍት በማዘጋጀት አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልጸው፤ በወጣት ማእከላትም መጻህፍትን በማቅረብ የንባብ ባህል እንዲያድግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኤጀንሲው የመጻህፍት እጥረት ባለባቸው ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶችና ቤተ መጻህፍቶች ክፍተቶችን እንደሚሞላ ባለሙያው አስታውቀዋል።
በንባብ ሳምንትና የመጻህፍት አውደ ርዕይ መርሐ ግብሩ መክፈቻ ላይ ደራሲያንና አርቲስቶች ተገኝተዋል።