ቀጥታ፡

የኮሮና ቫይረስ ስጋትን ለማስገንዘብ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23/2013 (ኢዜአ) ዜጎች የኮሮና ቫይረስ ስጋት መኖሩን ተገንዝበው ራሳቸውን እንዲጠብቁ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የድርሻቸውን እንዲወጡ የኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጥሪ አቀረበ። 

ኢኒስቲትዩቱ የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የኪነ ጥበብ ሙያተኞች ሚና ምን ሊሆን ይገባል? በሚለው ዙሪያ ከአርቲስቶች ጋር ተወያይቷል፡፡

በውይይቱ የቫይረሱ ስርጭት በዓለም፣ በአፍሪካና በኢትዮጵያ ስላለው ገጽታ ተብራርቷል። 


በተለይም አርቲስቱ ምን ሊሰራ ይገባል፣ ከማን ምን ይጠበቃል የሚል የውይይት መነሻ ጹሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።


የኢኒስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ በኀብረተሰቡ በኩል የኮሮና ቫይረስ መከላከል ላይ ከፍተኛ መዘናጋት እየታየ መሆኑን ተናግረዋል።


የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ፣ ርቀትን መጠበቅና በንጽህና አጠባበቅ ላይ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ገልፀው ይህም ቫይረሱ የደቀነውን ስጋት ካለመገንዘብ የመነጨ ነው ብለዋል።


በተካሄደ ጥናት እስከ 87 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ስለ ኮሮና ቫይረስ በቂ ግንዛቤ ቢኖራቸውም የጥንቃቄ እርምጃዎችን የሚወስዱት ግን ከ35 በመቶ እንደማይበልጡ ጠቁመዋል።


ባለፈው ነሃሴ በአዲስ አበባ ማስክ የሚጠቀመው ሰው 75 በመቶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ አስቻለው ይህ አሃዝ ወደ 54 በመቶ መውረዱ ኀብረተሰቡ ምን ያህል እየተዘናጋ እንደሆነ ያመላክታል ነው ያሉት።

በተመረጡ የክልል ዋና ዋና ከተሞች በተካሄደ ጥናትም ማስክ የማድረግ ምጣኔ ከ5 እስከ 15 በመቶ ብቻ መሆኑ አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ደግሞ በአሜሪካ፣ በአውሮፓና በደቡብ አፍሪካ  የመዛመት አቅሙ እስከ 70 በመቶ የሚደርስ አዲስ የቫይረሱ ዝርያ መከሰቱ ጉዳዩን አሳሳቢ እንዳደረገው ጠቁመዋል።

የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ዜጎች ግንዛቤ እንዲጨብጡ የሚጠበቅባቸውን መወጣታቸውን አስታውሰው ይህ ተግባራቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ኢኒስቲትዩቱ ቫይረሱን ለመከላከልና የዜጎችን ግንዛቤ ለማሳደግ ያለመ ለ6 ወራት የሚቆይ መርሃ ግብር መቅረጹንም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ አገልግሎት መስጠትም ሆነ መቀበል እንደማይቻል አስታውቀዋል፡፡

"ያገባኛል" በሚል መሪ ሀሳብ የፊት መሸፈኛ ያላደረጉ ዜጎች ላይ ቁጥጥር የሚደረግበት ስርዓት ይተገበራል ብለዋል።

መርሃ ግብሩ እንዲሳካ አርቲስቶች ትልቅ ሃላፊነት እንዳለባቸውም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ አቶ እንድርያስ ተረፈ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲነሳ ቫይረሱ የጠፋ እስኪመስል ድረስ መዘናጋት በመታየቱ ብዙ ስራ የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ በትራንስፖርት ቦታዎች በርካታ ሰዎች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንደማይጠቀሙ ጠቁመው የጥንቃቄ እርምጃዎቹን እንደከዚህ ቀደሙ በጥንቃቄ መተግበር አለባቸው ብለዋል።

ኅብረተሰቡን ለማስተማር የሚሰሩ የኪነ ጥበብ ስራዎችም ትክክለኛውን መልዕክት ማስተላለፋቸውን ማጤን ይገባል ነው ያሉት።

አርቲስቱ የኅብረተሰቡን እውቀት ለማጎልበት የሚሰራው ስራ ውጤታማ እንዲሆን የሚመለከታቸው አካላት ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ጀምሮ ድጋፍ ማድረግ አለባቸው ሲሉ ከኢትዮጵያ ፊልም ሰሪዎች ማኅበር የተወከሉት አቶ ደሳለኝ ሃይሉ ተናግረዋል።

"በእኛ በኩል የመስራት ተነሳሽነቱም አቅሙም አለ" ያሉት አቶ ደሳለኝ ስራዎችን ለማስኬድ ሰፊ በጀት ያስፈልጋል ለዚህም ዝግጁ መሆን ይጠይቃል ብለዋል። 

በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ከ84 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ሲያዙ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚሆኑት ለሕልፈት ተዳርገዋል።  

በኢትዮጵያም ከ124 ሺህ 264 በላይ ሰዎች በበሽታው ሲያዙ 1 ሺህ 923 መሞታቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም